ኢሳት (ሰኔ 6 ፥ 2008)
የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ገቢ ታክስ ለማሻሻል ሰሞኑን የቀረበው ረቂቅ አዋጅ የመንግስት የታክስ ገቢ በሶስት ቢሊዮን ብር እንዲቀንስ የሚያደርግ መሆኑ ተገለጠ።
ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ ሰራተኞች በየአመቱ ወደ አምስት ቢሊዮን ብር አካባቢ በገቢ ታክስ ሲከፍሉ መቆየታቸውን ያወሳው የገንዘብና የኢኮኖሚ ሚኒስቴር ረቂቅ አዋጁ የሚጸድቅ ከሆነ የሶስት ቢሊዮን ብር አካባቢ ገቢ መቀነስ እንደሚኖር አስታውቀዋል።
ይሁንና የሚኒስቴሮች ምክር ቤት በቅርቡ ባቅረበው በቀጣዩ አመት በጀት አመት ከደሞዝ ገቢ ግብር ወደ ስድስት ቢሊዮን ብር የሚደርስ ገንዘብ እንደሚሰበሰብ መግለጹ ይታወሳል።
በበጀት አመቱ ይገኛል የተባለው የደሞዝ ገቢ ግብር የደሞዝ ገቢ ታክስ ገቢን ታሳቢ ያደረገ ባለመሆኑ በበጀቱ ላይ ክፍተት ሊፈጠር እንደሚችል የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አስረድተዋል።
በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የህግ ክፍል ሃላፊ የሆኑት አቶ ዋሲሁን አባተ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ የሚጸድቅ ከሆነ በመንግስት የታክስ ገቢ ላይ የሶስት ቢሊዮን ብር ገቢ መቀነስ እንደሚኖር ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
ለቀጣዩ አመት እንዲጸድቅ ከቀረበው 274 ቢሊዮን ብር መካከል ወደ 20 ቢሊዮን የሚደርሰው ለደሞዝ እና የቀን ውሎ አበል ተከፋይ እንደሚደረግ ተገልጿል።
ረቂቅ አዋጁ በቀጣዮቹ ሳምንታት ውስጥ ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በገቢ ግብር ላይ የተደረገው ማሻሻያ በቂ እንዳልሆነ በመግለጽ ላይ መሆናቸውን ከሃገር በት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
በመካከለኛና በከፍተኛ የደሞዝ እርከን ላይ የሚገኙ ሰራተኞች በበኩላቸው የደሞዝ ገቢ ግብር ክፍያው የሃገሪቱን የዋጋ ግሽበትና የብር የመግዛት አቅም ያገናዘበ አይደለም ሲሉ በመግለጽ ላይ ናቸው።