የደህንነት አባላት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተገን በማድረግ ዘረፋ እየፈጸሙ ነው
በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ በሚገኙ አካባቢዎች የንብረት ዘረፋውም ተባብሶ ቀጥሏል
(ኢሳት ዜና የካቲት 20 ቀን 2010 ዓ/ም) በመዲናዋ አዲስ አበባ እና አዋሳኝ ከተሞች በቀንና በጨለማ ከፍተኛ የሆነ ዝርፊያ እየተፈጸመ ሲሆን የደህንነት አባላት እንዲሆኑ ራሳቸውን የሚገልጹ ሰዎች የዘረፋው ዋነኛ ተዋናዮች ሆነዋል። ዝርፊያው ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሱሉልታ፣ ሰበታ፣ ፉሪ፣ ቡራዩና በቅራቢያው በሚገኙ የገበሬ ማኅበራት ላይ የነዋሪዎች ቤት እየተሰበረ ዝርፊያ እየተፈጸመ ነው።
የንብረት ዘረፋው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላ በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠሉና ዘራፊዎቹም የነፍስወከፍ የጦር መሳሪያዎች መታጠቃቸው እንዲሁም ራሳቸውን የደህንነት አባላት ነን በማለት መግለጻቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ነዋሪ ሲናገር “ የግል ተሽከርካሪ ይዞ ወደ መኖሪያ ሰፈሩ በመግባት ላይ ያለ ግለሰብ፣ የፖሊስ ፒክ አፕ መኪና በያዙ ፖሊሶች በድንገት እንዲቆም ይደረጋል። አንዱ ፖሊስ በፍጥነት ወርዶ መታወቂያ ያሳይና ግለሰቡን “አሸባሪ ነህ” ይለዋል፤ ግለሰቡም ሰላማዊ መሆኑን በድንጋጤ ስሜት ውስጥ ሆኖ ለማስረዳት ሞከረ፣ ጭቅጭቁ ሲበዛ ፖሊሱ 400 ብር አምጣ ብሎ ይጠይቀዋል። ግለሰቡም 500 ብር ሰጥታቸውና ሁሉም ሄዱ” ብሎአል። ከፖሊሶች መካከል አንደኛው ማዕረግ ያለው መሆኑን የአይን እማኞች ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ዙሪያ የአርሶ አደሩን መሬት በሕገወጥ መንገድ ተቀራምተው የነበሩ የአገዛዙ ካድሬዎች፣ ባለሃብቶችና ደጋፊዎች ንብረቶቻቸውን በመሸጥና በማከራየት ከአካባቢው እየወጡ በመሆኑ፣ የመኖሪያ ቤት፣ የመሬት ዋጋ ና የቤት ኪራይ ዋጋ እየቀነሰ መምጣቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።