የደህንነት መስሪያ ቤት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች ከአገር እንዳይወጡ አዘዘ

የካቲት 18 ቀን 2005 ዓ/ ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ አየር መንገድ 15 የትኬት እና 30 የኤርፖርት ሰራተኞችን ከስራ ካባረረ በሁዋላ ከአገር እንዳይወጡ አገደ። ከአየር መንገድ የውስጥ ምንጮች የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ሀብታሙ ጫኔ፣ ዳንኤል ገበየሁ፣ ኢማን ያሲን፣ ኤደን ካሳየ፣ ቤዛ ኤፍሬም፣ ይገርማል ታደሰ፣ ሰለሞን ይብራህ፣ ክንፈ ሚካኤል ሽጉጤን ጨምሮ በርካታ ሰራተኞች ከስራ የተባረሩ ሲሆን ፣ አየር መንገዱ ለደህንነት እና አሚግሬሽን መስሪያ ቤት በጻፈው ደብዳቤ ሰራተኞቹ ከአገር እንዳይወጡ አሳግዷል።

ሰራተኞቹ ከአገር እንዳይወጡ ሲታገዱ ከተዘረዘሩት ምክንያቶች መካከል ለህዳሴው ግድብ ገንዘብ ለማዋጣት ፈቃደኛ አለመሆን፣ የድርጅቱን ሚስጢራዊ መረጃዎች የአገር ጠላት ለሆኑት የሽብርተኞች ሚዲያዎች ለኢሳት እና ለፍትህ ጋዜጣ መስጠታቸው፣ እንዲሁም የባለራእዩን መሪ የአቶ መለስ ዜናዊን ራእይ ለማሳካት በሚል የተነደፈውን የስድስት ቀን የነጻ የስራ አገልግሎት እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ  ፈቃደኛ አለመሆን የሚሉት ይገኙበታል። የሰራተኞቹ ፓስፓርት ቁጥር ለኢሚግሬሽንና ደህንነት ክፍል በመላኩ ሰራተኞች ከአገር ለመውጣትና ራሳቸውን ለማዳን አልቻሉም።

ከዚህ ቀደም ከስራ ከተባረሩት መካከል ከሙስሊሙ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የታሰሩት ሰባ ማይልስ ስራ አስኪያጅ እስካሁን አልተፈቱም።

አካሉ አሰፋ፣ አንተሰናይ አማረ፣ ቤተልሄም ተፈራ፣ ቤተልሄም ጌታቸው፣ ኤደን በየነ፣ ኤደን ካሳየ፣ ኢማን ያሲን፣ ሳሙኤል እንዳለ፣ ሶሎሞን በቀለ፣ አይዳ ዘልኡል፣ አማኑኤል በልስቲ፣ አማኑኤል ነጋሽ፣ አማኑኤል ጸጋው፣ አንዱአለም ግርማ፣ ብርሀኑ ሰሎሞን፣ ቸርነት አለሙ፣ እኑ ገብረእግዚአብሄር፣ ሀይማኖት ንጉሴ፣ ሂሩት መለሰ፣  ቅድስት አበራ፣ ቅድስት ከበደ፣ ማትያስ አድማሱ፣ መቅደስ አበራ፣ ሜላት አስራት፣ ትንግርት ደምሴ፣ ሳምራዊት ገረመው፣ ሰሚራ አማን፣ ተዘራ ወርቁ፣ ወንዶሰን ሀብቴ፣ ዮሀንስ ፍሰሀ እና አልአዛር ተክለ ሚካኤል ከአገር እንዳይወጡ ትእዛዝ ከተላለፈባቸው መካከል ይገኛሉ።

የተባረሩ ሰራተኞችን በተመለከተ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ አስኪያጅን ለማነጋገር ተደጋጋሚ የስልክ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም። አየር መንገዱ ነባር ሰራተኞችን እያባረረ በታማኝ የኢህአዴግ አባላት እየተካ መሆኑን በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል።