የደህንነት መስሪያ ቤቱ የነጻነት ታጋዮችን በድለላ ለማስገባት የጀመረው ጥረት እስካሁን ውጤት አላመጣም

ጥቅምት ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በሰሜን ጎንደር ዞን ባሉ በረሃዎች የሚንቀሳቀሱ በርካታ የነጻነት ሃይሎችን በማታለል እጃቸውን ለህወሃት/ኢህአዴግ ሹሞች እንዲሰጡ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት  የነጻነት ሃይሎች ውድቅ አድርገውታል።

ከወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ አቅራቢዎች ጋር በተያያዘ አገዛዙ የወሰደው እርምጃ በርካታዎች ጫካ እንዲገቡ አድርጓቸዋል። በጎንደር የተካሄዱትን ታውሞዎች ተከትሎም፣ ብዙ ወጣቶችና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጫካ የገቡ ሲሆን፣ በአገዛዙ ወታደሮችና ድርጅቶች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲያደርሱ ቆይተዋል። እነዚህን ሃይሎች አድኖ ለመያዝ ያደረገው ሙከራ ያልተሰካላት አገዛዙ፣ በአካባቢው ሰዎች አማካኝነት የሽምግልና ጥረቱን ከጀመረ ከሁለት ሳምንታት በላይ ሆኖታል።

“የወንድማማቾች ደም ሊፈስ አይገባውም፣ መንግስት ምህረት ያደርግላችሁአል፣ የፈለጋችሁት ነገርም ይደረግላችሁዋል” የሚል መልዕክት በአካባቢው ሹሞችና አንዳንድ የአገር ሽማግሌዎች በኩል ቢቀርብም፣ ታጋዮቹ ግን በፍጹም አልተቀበሉትም።

በሌላ በኩል ጥቅምት 20 ቀን 2009 ዓም በዚሁ ዞን በዳባት ወረዳ ደጋ መረባ አካባቢ የሚገኙ የነጻነት ታጋዮችን ለማጥቃት በሁለት ኦራል መኪኖች የተጫኑት ወታደሮች ያልተጠበቀ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ታጋዮቹ ባካሄዱት የደፈጣ ተኩስ ፣ ሁለት ወታደሮችን ገድለው አምልጠዋል። በታጋዮች በኩል የደረሰ ጉዳት የለም። በዚሁ ደንገተኛ ጥቃት የተደናገጡት ወታደሮች አካባቢውን ለቀው መውጣታቸው ታውቋል።