ኢሳት (ሚያዚያ 7 ፥ 2008)
ከአንድ አመት በፊት ስልጣናቸውን ተጠቅመው ሙስና ፈጽመዋል ተብለው በቁጥጥር ስር የዋሉት የቀድሞ የሃገር ውስጥ የደህንነት ሃላፊ በሰባት ክሶች ጥፋተኛ ተባሉ።
የደህንነት ሃላፊ የነበሩት አቶ ወልደስላሴ ወልደሚካዔል በስልጣን ላይ በነበሩ ጊዜ የተለያዩ ሙስናዎችን ፈጽመዋል ተብለው 12 ክሶች ተመስርቶባቸው እንደነበር ይታወሳል።
የተከሳሹን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አርብ በሰጠው ውሳኔ አቶ ወልደስላሴን በሰባት ክሶች ጥፋተኛ ሲል ብይን መስጠቱን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
የተከሳሹ አንድ ወንድምና እህትም ተባብረው ተገኝተዋል በሚል በሶስት ክሶች ጥፋተኛ የተባሉ ሲሆን ተከሳሽ በስልጣን ዘመናቸው በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብን ያለ አግባብ አፍርተዋል ተብሎ ክስ ቀርቦባቸው መቆየቱ ይታወቃል።
ምንጩ ያልታወቀ ሃብትን አፍርተዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው የሚገኙትና የጥፋተኝነት ብይን የተላለፈባቸው አቶ ወልደስላሴ የቀረበባቸው የሙስና ክስ በማስተባበል የተለያዩ መቃወሚያዎችን ሲያቀርቡ መቆየታቸውንም የተከሳሹ ጠበቆች ይገልጻሉ።
የጥፋተኝነት ብይንን የሰጠው የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የአቃቤ ህግና ተከሳሾችን የቅጣት ማቅለያና ማክበጃ ለማድመጥ ለሚያዚያ 12 2008 አም ተለዋጭ ቀጠሮን መስጠቱም ታውቋል።