(ኢሳት ዜና–ሕዳር 18/2010)የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የነበረው ዮናታን ተስፋዬ ተከሶበት የነበረው የሽብር ተግባር ክስ ተሰረዘለት።
ክሱ ወደ መደበኛ ወንጀል የተቀየረው የፍርድ ሂደት የዮናታን የእስር ቤት ቆይታንም ከ6 አመት ወደ 3 አመት ዝቅ እንዲል አድርጎታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የወልቃይት አማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት ዳኛ ዘርአይ ወልደሰንበት ከችሎት እንዲነሱላቸው ለፍርድ ቤት ያቀረቡትን አቤቱታ በፅሁፍ ማስገባታቸው ታውቋል።
በታህሳስ 2008 ነበር በኦሮሚያ ከተቀሰቀሰው አመጽ ጋር ግንኙነት አለህ፣አመጹን በማህበራዊ ድረገጾች ላይ በማሰራጨት ተሳትፈሃል፣በሽብር ተግባር ውስጥም እጅህ አለበት በሚል ወደ ዘብጥያ እንዲወርድ የተደረገው።-በማህበራዊ ድረገጾች አክቲቪስትነት የሚታወቀውና የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የነበረው ዮናታን ተስፋዬ።
ከዚህም ጋር ተያያዞ ነበር በወቅቱ የተሰየመው ችሎት እነ ዮናታን ያቀረቡትን የመከላከያ ነጥብ ወደ ጎን በማለት የጥፋተኝነት ብይንን ያሳለፈበት።
ውሳኔውም 6 አመት ከ6 ወር በእስር ቤት እንዲያሳልፍ የሚያዝ ነበር።
ዮናታን ተስፋዬ በተደጋጋሚ በጠበቃው አማካኝነት ባቀረበው የይግባኝ ጥያቄ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት በዮናታን ተስፋዬ ላይ ተላልፎ የነበረውን በሽብር ተግባር ውስጥ ተሳትፈሃል በሚል አሳልፎት የነበረውን ብይን በመሰረዝ ወደ መደበኛ ክስ እንዲቀየር አድርጓል።
6 አመት ከ6 ወር ተወስኖበት የነበረውን የእስር ቤት ቆይታውንም ወደ 3 አመት ከ6 ወር እንዲቀነስለት ውሳኔ አሳልፏል።
ዛሬ በፍርድ ቤቱ የተሰጠው ብይን 3 አመት ያህል በእስር ቤት ሲማቅቅ የከረመው ዮናታን ተስፋዬ በቅርቡ ከእስር እንዲወጣ ያስችለዋል ይላሉ ምንጮች።ሌላ ተያያዥ ጉዳይ ተፈልጎለት በዛው እንዲከርም ካልተደረገ የሚሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የፍትህ ስርአት ላይ እምነት የሌላቸው ባለሙያዎች ናቸው።
የህግ ባለሙያዎች ቀደሞውኑ ዮናታን በሽብር ተግባር ሲከሰስ የቀረቡት ማስረጃዎች አሳማኝ ናቸው በሚል የእስር ብይን እንዲተለለፍበት ተደርጓል።
አሁን ደግሞ በሽብር ተግባር ውስጥ እጅህ የለበትም ከዚህ ጋር ተያይዞም የእስር ዘመንህ ተቀንሶልሃል መባሉ በፖለቲካ የሚቃኙት የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ሂደት ምን እንደሚመስል ማሳያ ነው ይላሉ ባለሙያዎቹ።
በየፍርድ ቤቶች የሚሰጠው አላግባብ የሆነ ብይንና የዜጎች የእስር ቤት ስቃይ የሚፈጠረውም በእንደዚህ አይነቱ የህግ ስረት ነው ሲሉም ያክላሉ።
ለዚህ ማሳያ አድርገው የሚያቀርቡት በየጊዜው ከታሳሪዎች የሚሰሙ ሮሮዎችንና አላግባብ የሆኑ ስቃዮችን ነው።
በቅርቡ ችሎት በመቅረብ በደሉ በዛብኝ የእስር ቤቱ ስቃይም አንገላታኝ ፣የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረደኝ ሲል በእስር ቤት እንዲኮላሽ መደረጉን ልብሱን በአደባባይ አውልቆ ያሳየው ታሳሪም ጉዳይ የሰለባዎቹ መገለጫ ነው ሲሉ ያክላሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የወልቃይት አማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት ዳኛ ዘርአይ ወልደሰንበት ከችሎት እንዲነሱላቸው ለፍርድ ቤት ያቀረቡትን አቤቱታ በፅሁፍ እንዲያስገቡ በታዘዙት መሰረት ማመልከቻቸውን ማስገባታቸው ታውቋል።
የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት አቶ መብራቱ ጌታሁን ፣ አቶ ጌታቸው አደመ ፣ አቶ አታላይ ዛፌ ፣ አቶ አለነ ሻማና አቶ ነጋ ባንተይሁን ባቀረቡት ማመልከቻ ዳኛው ዘርአይ ወልደሰንበት በወልቃይት የአማራ ማንነት ላይ ግልጽ የሆነ የፖለቲካ አቋማቸውን የሚያራምዱ መሆናቸውን በተለያዩ መድረኮች ሲያንጸባርቁ ታይተዋል።
የህወሃት አባል እንደሆኑ የሚታወቁት እኚሁ ዳኛ በሽብር ክስ ከከሰሳቸው አቃቢ ሕግ የተለዩ ባለመሆናቸው ከእሳቸው ፍትሕ እንደማይጠብቁና ስለዚም ዳኛው ይቀየሩላቸው ዘንድ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት የተጻፈውን 46 ገጽ ጽሁፍ አባሪ በማድረግ ማመልከቻቸውን ማቅረባቸው ታውቋል።