የዞን 9 ጦማርያን ሌላ ቀጠሮ ተሰጠባቸው

ሐምሌ ፲፫ (አስራሶስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው የሚገኙት የዞን 9 ጦማርያን ሐምሌ 13/2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።
በእስር ላይ የሚገኙት በፍቃዱ ኃይሉ፣ አጥናፍ ብርሃኔ፣ ናትናኤል ፈለቀ እና አቤል ዋበላ ለ31ኛ ጊዜ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን የዘገበው ጋዜጣው፣ መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረው ተከሳሾች የቀረበባቸውን ክስ ይከላከሉ ወይስ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ ይሰናበቱ በሚለው ላይ ብይን ለመስጠት ነበር፡፡
“ፍርድ ቤቱ ግን የአቃቤ ህግ የደረጃ ምስክሮች ቃል በጽሑፍ ተገልብጦ ከመዝገቡ ጋር አለመያያዙን በመግለጽ ውሳኔ እንዳልሰጠ አስረድቷል፡፡”
በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ለሐምሌ 22/2007 ዓ.ም የምስክሮች ቃል በጽሁፍ ተገልብጦ ከመዝገቡ ጋር መያያዙን ለመጠባበቅ ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል፡፡
ቀሪዎቹ የዞን 9 አባላትና ጋዜጠኞች በመንግስት ቀጥተኛ ትእዛዝ እንዲፈቱ መደረጉ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የፍትህ ስርአት ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ እንደሚያስገባው የተለያዩ አለማቀፍ ሚዲያዎች ሲዘግቡ ሰንብተዋል።