የዞን 9 ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ የዋስ መብቱ ሲፈቀድለት የሎሚ መጽሔት አዘጋጅ በሌሉበት 18 ዓመት ተፈረደባቸው

ጥቅምት ፲ (አስር) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አንድ ዓመት ከአምስት ወር በሽብር ክስ ተከሰው በእስር ሲንገላቱ የነበሩት የዞን 9 አምደ መረብ ጸሐፍት ውስጥ ብቻውን እንዲቀር ተደርጎ የነበረው ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ ክሱን ውጪ ሆኖ እንዲከታተል የሃያ ሽህ ብር የዋስትና መብት የልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት19ኛ ወንጀል ችሎት በመፍቀዱ ከእስር ተለቋል።
በተጨማሪም የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ስምንተኛ የወንጀል ችሎት የሎሚ መጽሄት ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ታዬ ግዛውን በሌሉበት የአስራስምንት ዓመት ጽኑ እስራት ፈርዶባቸዋል።ጋዜጠኛ ታዬ ግዛው ከዚህ ቀደምም አመጽ በማነሳሳት ክስ ተወንጅለው በሃምሳ ሽህ ብር ዋስ የተፈቱ ሲሆን ጋዜጠኛው የስራ ነጻነት በማጣታቸው ተሰደዋል።
በኢትዮጵያ ሕግን ከለላ በማድረግ ዜጎችን ካለ ፍትሕ ማንገላታትና ማጥቃት የተለመደ አሰራር እየሆነ የመጣ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝን ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት ”ከበቂ በላይ መረጃዎች በእጃችን አለን!” በማለት በዓደባባይ መግለጫዎችን ሲሰጡ ቢከርሙም ጦማሪያኑ ላይም ሆነ ጋዜጠኞቹ ላይ ሕግን በመተላለፍ የፈጸሙት ጥፋት እንደሌለ የህግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ገዢው መንግስት ጋዜጠኞች፣የሰብዓዊ መብት ተሟጓቾች፣ሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላትን፣ የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን ጨምሮ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ በነጻ ሊያሰናብታቸው እና ለደረሰባቸው ጉዳት የሞራል ካሳ ሊከፍላቸው ይገባል የሚሉት ባለሙያዎች፣ እንዲሁም በንጹሃን ዜጎች ላይ በሃሰት የመሰከሩና አካላዊና ሞራላዊ ጉዳት የፈጸሙትም በሕግ ፊት መጠየቅ አለባቸው ሲሉ ያክላሉ።