ኢሳት (ህዳር 2 ፥ 2009)
የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን የሆነው በፍቃዱ ሐይሉ አርብ ህዳር 2 ቀን 2009 አም ከጠዋቱ 12 ሰዓት አካባቢ በመኖሪያ ቤቱ እያለ “ኮማንድ ፖስቱ ሊያናግርህ ይፈልጋል” በሚል ሲቪል በለበሱ የፀጥታ ሃይሎች መወሰዱን የአገር ቤት ምንጮቻችን ለኢሳት ገልፀዋል።
ከሌሎች የዞን ዘጠኝ ጦማሪያዎችና ጋዜጠኞች ጋር በመሆን ለአንድ አመት ከስድስት ወር የእስር ቆይታ በኋላ በዋስ የተለቀቀውና አቃቤ ህግ ይግባኝ የጠየቀበት ጦማሪ በፍቃዱ ሐይሉ በፀጥታ ሃይሎች ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ መጀመሪያ በአከባቢው በሚገኘው ወረዳ 6 የፖሊስ ንዑስ ጣቢያ እንዲቆይ ተደርጎ ከሰአት በኋላ የካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዱን ምንጮቻችን አክለው ገልፀዋል።
የዞን ዘጠኝ አባል የሆነው ዘላለም ክብረት በትዊተር ገጹ ላይ “የፀጥታ ሃይሎች ጦማሪ በፍቃዱን በቁጥጥር ስር ካዋሉት በኋላ ያሰሩበት ምክንያት በኦክቶበር 31 ቀን 2016 ከአሜሪካን ድምጽ አማርኛው ዝግጅት ቃለ-መጠይቅ በመስጠቱ እንደሆነ ገልጸውለታል” በማለት ገልጿል።
ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ ከእስር ከተፈታ በኋላ “ውይይት” በሚባል ወርሃዊ መጽሔት ላይ በዋና አዘጋጅነት እየሰራ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ ከ4 ቀን በኋላ ህዳር 6 ቀን 2009 ዓ.ም አቃቤ ህግ በዋስ የተለቀቀበትን በይግባኝ ለአምስተኛ ጊዜ እንዲታይለት ቀጠሮ መያዙ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ለፕሬስ ነፃነት ላበረከቱት አስተዋጽኦ በአሜሪካን ኒውዮርክ ከተማ “የአለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ሽልማት” ከሲፒጄ እና በሲውዘርላንድ ጄኔቫ “የማርቲን ኢናልስ 2016” ሽልማት ማግኘታቸው የሚታወስ ነው።