ጥር ፳፮(ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ላለፉት 9 ወራት በ እስር ላይ ይሚገኙት የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ጋዜጠኞች ሰብሳቢ ዳኛው ከችሎት እንዲነሱ ጠየቁ፡፡
ጦማርያኑና ጋዜጠኞቹ ለ17ኛ ጊዜ ጥር 26/2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ልደታ ምድብ ቸሎት ሲቀርቡ በጽሁፍ ባቀረቡት አቤቱታ፦ የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ የሆኑት አቶ ሸለመ በቀለ ፦‹‹የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብታችንን አላስከበሩልንም›› በማለት ከችሎት እንዲነሱ ጠይቀዋል፡፡
ዳኞቹ በሰጡት ምላሽ -ፍርድ ቤቱ የተሰየመው “ተሻሽሎ ቀርቧል” በተባለው የአቃቤ ህግ ክስ ላይ የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመስማት እንደሆነ ቢናገሩም፣ ጦማርያኑና ጋዜጠኞቹ አቤቱታቸው ሳይሰማ የእምነት ክህደት ቃል ለመስጠት ዝግጁዎች አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኛ በሰብሳቢ ዳኛው ላይ አቤቱታ አለን፤ ፍርድ ቤቱ የራሱን ውሳኔ እንኳ አላከበረም፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን የእምነት ክህደት ቃላችንን ለመስጠት ዝግጁዎች አይደለንም›› ነው ያሉት ተከሳሾቹ።
ዳኛ ሸለመ በቀለም፦ ‹‹የእኛን ውሳኔ የማትቀበሉ ከሆነ ፤ጉዳዩን በይግባኝ እንዲታይ ማድረግ ይቻላል›› በማለት መልሰዋል። ዳኛው ይህን ቢሉም ጦማርያኑ በጽሁፍ ባቀረቡት አቤቱታ፦‹‹ላለፉት ስድስት ወራት በነበረው የክርክሩ ሂደት የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ አቶ ሸለመ በቀለ ሂደቱን በአግባቡ በመምራት የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብታችንን አላስጠበቁልንም፡፡ በተለያየ ጊዜም ሐሳባችን ለመግለጽ ስንሞክር ክልከላ አድርገውብናል፡፡ አሁን ደግሞ ችሎቱ ራሱ የሰጠውን ትዕዛዝ ራሱ ሽሮ ፈጽሞ ልንረዳው በማንችለውና የመከላከል መብታችንን በሚያጣብብ የክስ ሁኔታ ክርክሩን እንድንቀጥል ሲበየንብን የችሎቱ ሰብሳቢ ወሳኝ ሚና ነበራቸው›› ብለዋል። በመሆኑም ሰብሳቢ ዳኛው ከችሎቱ እንዲነሱላቸው ተከሳሾቹ ጠይቀዋል።
ፍርድ ቤቱም፤ የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ አቶ ሸለመ በቀለ ከችሎት እንዲነሱ የሚጠይቀውን አቤቱታ አይቶ ነገ ብይን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡