ኢሳት (ጥቅምት 2 ፥ 2009)
ባለፈው አመት ከ18 ወራት እስራት በኋላ ከተመሰረተባቸው የሽብርተኛ ወንጀል ክስ በነጻ የተሰናበቱ የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን የዘንድሮው የማርቲን ኤናልስ ሶስት አሸናፊዎች መካከል አንዱ በመሆን ማክሰኞ በስዊዘርላንድ ሽልማትን ተቀበሉ።
ይኸው አመታዊ ሽልማት አስር ታዋቂ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በጋራ የሚያዘጋጁት ሲሆን ሽልማቱ ለሰብዓዊ መብት መከበር ጥረት ላደረጉ አካላት የሚበረከት መሆኑ ታውቋል።
ከዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ጋራ የክብር ሽልማቱን ለማግኘት ከበቁት በእድሜ ልክ እስር ላይ የሚገኘውና በሰብዓዊ መብት ተጓጋችነቱ የሚታወቀው ኢልሃም ቶቲ እንዲሁም በሶሪያ አማጽያን የተጠለፈችው ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ራሳን ዘይቱን መሆናቸውን የሽልማቱ አዘጋጆች አስታውቀዋል።
የሽልማቱ ስነስርዓት ጀኔቭ ስዊዘላንድ በሚገኘው የጄኔቭ ዩኒቨርስቲ በደማቅ ሁኔታ የተካሄደ ሲሆን፣ ጦማሪ ዘላለም ክብረት የዞን ዘጠኝ አባላትን በመወከል ሽልማቱን ተረክቧል።
የዞን 9 አባላት ከተመሰረተባቸው የሽብርተኛ ወንጀል ክስ በነጻ ቢሰናበቱም አሁንም ድረስ ከሃገር እንዳይወጡ እገዳ ተጥሎባቸው እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል።
ሶሪያዊቷ ጋዜጠኛ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች በሃገሯ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለአለም በማቅረብ የምትታወቅ ሲሆን፣ ከሁለት አመት በፊት ከባለቤቷ ጋርና ከባልደርቦቿ ጋር ከቢሮዋ ታግታ ከተወሰደች በኋላ እስካሁን ድረስ ያለችበት ሁኔታ አይታወቅም።
በእድሜ ልክ እስር ላይ የሚገኘው ምሁሩ ቻይናዊ ኢልሃም ቶቲ ለበርካታ አመታት በሚጽፋቸው ጽሁፎች በሃገሩ መንግስት እንግልት ሲደርስበት እንደነበር አዘጋጆቹ ስለተሸላሚዎቹ ካሰራጩት መረጃ መረዳት ተችሏል።