ነኅሴ ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ኤልኒኖ ከግንቦት ወር 2007 ዓ.ም ጀምሮ በመከሰቱ በኢትዮጵያ በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች የዝናብ ስርጭት መዛባት መከሰቱን፣ ከዚሁ ችግር ጋር ተያይዞ በቀጣይ ሁለት ወራትም የዝናብ መዛባቱ እንደሚቀጥል ይፋ አድርጓል።
የኤጀንሲው ሃላፊዎች ትላንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በግንቦትና በሰኔ ወራት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተሻለ ዝናብ የነበረ ቢሆንም በሐምሌ ወር የክረምት ዝናብ ሰጪ ክስተቶች በከፍተኛ ደረጃ መዳከማቸውን አስረድተዋል፡፡
በዚህም ምክንያት በአማራ፣ በኦሮሚያ ምስራቃዊ አጋማሽ ፣ በድሬዳዋ፣ በሀረሪ እና በሱማሌ አካባቢዎች ዝናቡ መደበኛውን ፈር በተከተለ መልኩ አለመጀመሩን አስታውቆአል፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 መጀመሪያ ጀምሮ ቀስ በቀስ መሞቅ የጀመረው የትሮፒካል ፓስፊክ ውቅያኖስ የላይኛው የውሃ ክፍል እየተጠናከረ ሄዶ የኤልኒኖ ክስተት መፍጠሩን ኤጀንሲው ገልጾአል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የኤልኒኖ ክስተት እየተጠናከረ በመምጣቱ በቀሪዎቹ የክረምት ወራት ማለትም በነሃሴና በመስከረም በመደበኛ ሁኔታ የሚኖረው የዝናብ መጠንና ስርጭት የተዛባና ያልተስተካከለ እንደሚሆን፣ በምዕራብ የሀገሪቱ አጋማሽ ላይ የተሻለ ዝናብ ቢኖርም ዝናቡ በቦታና በጊዜ ስርጭት ያለመስተካከል እንዲሁም በአዘናነብና በመጠን ረገድ ከፍተኛ የመዋዥቅ ባህርይ ሊያሳይ እንደሚችል ይጠበቃል ሲሉ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
የወቅቱ የዝናብ አወጣጥን በተመለከተ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ ከሆኑት አንዳንድ የሀገሪቱ ሰሜናዊ አጋማሽ ላይ አወጣጡ ከመደበኛው ጋር ያለመስተካከልና ወጣ ገባ የማለት ገጽታ ሊኖረው እንደሚችል ይጠበቃል ሲል ኤጀንሲው አክሏል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከመስከረም ወር መጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ የክረምቱ ዝናብ ከአፋርና አጎራባች ከሆኑት የትግራይና አማራ ምስራቃዊ ክፍሎች ላይ የሚያቆም ይሆናል ብሎአል፡፡
የዘንድሮው የክረምት ዝናብ ከመደበኛው ጋር ያለመስተካከል ጋር ተያይዞ በግብርና ፣ በውሃ እና በጤና ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ በዚሁ መግለጫው በደፈናው ጠቁሞአል፡፡