(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 25/2011) በሃገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የዜጎችን ህይወት ያጠፉ፤ የአካል ጉዳት ያደረሱና ንብረት ያወደሙ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ መንግስት ርምጃ እንዲወስድ ተጠየቀ፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዜጎች ላይ የህይወትና የንብረት ጉዳት ያደረሱት አካላት ላይ የሚወሰደው ርምጃ ፈጣን እንዲሆን በዛሬው ዕለት አሳስቧል፡፡
መንግስት በበኩሉ ህዝብ ላይ ጉዳት ያደረሱ ከ600 በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማድረጉን አስታውቋል፡፡
በተያያዘ ዜና በኢትዮጵያ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ መፈናቀሉን በመንግስት የተቋቋመ አንድ ግብረሃይል ይፋ አድርጓል።
በአራት ክልሎች የመስክ ጥናት አድርጎ የተመለሰው ግብረሃይል ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት ከተፈናቀሉት መካከል ከ700 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ገልጿል፡፡
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራው ግብረሃይል በኦሮሚያ፣ በ አማራ፣ በደቡብና በትግራይ ክልሎች ያደረገውን የመስክ ጥናት ሪፖርት በዛሬው ዕለት አቅርቧል።
በጽሁፍና በድምጽ የተጠናቀረው የግብረሃይሉ ሪፖርት በተፈናቀሉ ዜጎችና በህዝብ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን በተመለከተ ያሉት መረጃዎች ተሰብስበው መቅረባቸውን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመላክተው።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበለትን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ መንግስት በዜጎች ላይ ግድያ፤ ዘረፋና የንብረት ማውደም ተግባር የፈጸሙ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ አፋጣኝ ርምጃ እንዲወስድ ነው ያሳሰበው።
በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የቀጠለው አለመረጋጋት የግለሰቦችና ቡድኖች እጅ በቀጥታ ያለበት መሆኑን ያወሳው የተወካዮች ምክር ቤት ህጋዊ የሆነ ርምጃ ካልተወሰደ ችግሩ እየከፋ ሊመጣ እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል።
በሁሉም ክልሎች መንግስት አጥፊዎችን ለይቶ ለህግ የማቅረብ ስራ ላይ ሊያተኩር እንደሚገባ ቡድኑ የመፍትሄ ሀሳብ አስቀምጧል፡፡
በምክር ቤቱ ተገኝተው ሪፖርት ያቀረቡት የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፍሪያት ካሚል እስካሁን ከ600 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።
ከእነዚህም 400 የሚሆኑት በፍርድ ሂደት ላይ እንደሆኑም ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።
በመንግስት በኩል የተላከው ግብረሃይል ተፈናቃዮችንም የተመለከተ ዝርዝር ምልከታውን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።
በአራቱ ክልሎች በሚገኙ 13 ዞኖች ስር ያሉ 27 መጠለያ ጣቢያዎችን ተዘዋውረው ጥናቱን ያደረጉት የግብረሃይሉ አባላት በኢትትዮጵያ በአጠቃላይ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃይ እንደሚገኝ ነው በሪፖርቱ ያመለከቱት።
በትግራይ 111 ሺህ 465፣ በደቡብ 873 ሺህ 22፣ በኦሮምያ 1 ሚሊየን 720 እንዲሁም በአማራ 107 ሺህ ህዝብ መፈናቀሉን የግብረሃይሉ ሪፖርት ያመለክታል።
በሰላም ሚኒስትሯ በቀረበው ሪፖርት ደግሞ ከእነዚህ ተፈናቃዮች መካከል ከ700ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ቀዬአቸው መመለሳቸውን የሚያሳይ ነው።
መፈናቀሎቹ የተከሰቱት በየአካባቢዎቹ በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያትና በተፈጥሮ አደጋ መሆኑን የገለጸው ግብረሃይሉ በመንግስት በኩል የሚደረገው ጥረት በአቅም ውስኑነት የተነሳ በሚፈለገው ደረጃ እየተከናወነ አይደለም ብሏል።