የዚምባቡዌ ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ በመጪው ምርጫ ካሸነፉ ቻይናውያን ባለሀብቶችን ከሀገራቸው ጠራርገው እንደሚያስወጡ አስታወቁ።

የዚምባቡዌ ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ በመጪው ምርጫ ካሸነፉ ቻይናውያን ባለሀብቶችን ከሀገራቸው ጠራርገው እንደሚያስወጡ አስታወቁ።
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 24 ቀን 2010 ዓ/ም) በመጪው ሐምሌ በዚምባቡዌ በሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ግምት ከተሰጣቸው ዋነኛ ተፎካካሪዎች መካከል አንዱ- የዋኘኛው ተቃዋሚ ፓርቲ የዲሞክራቲክ ለውጥ ንቅናቄ መሪ ናቸው።
ሚስተር ኔልሰን ቻሚሳ ለምርጫው እያደረጉት ባለው ቅስቀሳ “በምርጫው ካሸነፍን ሁሉንም የቻይና ኩባንያዎች እናባርራቸዋን”ማለታቸውን አንድ የዚምባቡዌ የግል ድረ ገጽን ዋቢ በማድረግ ቢቢሲ ዘግቧል።
ቻሚሳ አክለውም ፦” ከቻይናውያን ኩባንያዎች ጋር ሕዝባችንን ትርፋማ የሚያደርግ አዲስና ግልጽ ውል እንፈልጋለን”ብለዋል።
ባለፈው የካቲት ሞርጋን ዝቫንጊራይ ማረፋቸውን ተከትሎ ነው ሚስተር ቻሚሳ የዲሞክራቲክ ለውጥ ንቅናቄ ፓርቲ መሪነትን የተረከቡት።
ይሁንና በፓርቲው ውስጥ በቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በቶኮዛኒ ኩፔ የሚመራ አንጃ በመፈጠሩ የቻሚሳ አመራር አደጋ እንደተጋረጠበት ይነገራል።
በመጪው ሐምሌ በዚምባቡዌ የሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሀገሪቱን አርባ ለሚጠጋ አመታት ሲገዙ የቆዩት ሮበርት ሙጋቤ ባለፈው ህዳር ከተወገዱ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድ ነው።
ፕሬዚዳንት ኢመርሰን ምናንጋግዋ ገዥውን ዛኑ ፓርቲን በመወከል ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር የሚያስችላቸውን ትኬት ቆርጠዋል።.
እንደ ቻይና የመሣሰሉት የምሥራቅ ሀገራት ኢኮኖሚ ፖሊሲ አድናቂ በመሆናቸው የሚታወቁት ምናንጋግዋ፣ ከሙጋቤ ሥልጣን ከተረከቡ ወዲህ ምዕራባውያን ባለሀብቶችን ወደ ሀገራቸው እየጋበዙ ይገኛሉ።
የተቃዋሚ ፓርቲው ቻሚሳ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ በምርጫ ቅስቀሳቸው ባደረጉት ንግግር “ፕሬዚዳንት ምናንጋግዋ ኢኮኖሚያዊ ውል የገቡት የሀገሪቱን ሀብት በማራቆት ላይ ከተጠመዱት ቻይናውያን ጋር እንደሆነ አስተውለናል” ማለታቸውን መንግስታዊው ሄራልድ ጋዜጣ አስነብቧል።
ቻሚሳ አክለውም፦”ባለፈው መስከረም ወር ገና ሥራዬን ስጀምር ቻይናውያን ከሀገራችን ጋር የገቡት ውል ተቀባይነት እንደሌለው እና ሀገራችንን ለቀው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ነግሬያቸዋለሁ”ብለዋል።
ቻይና- ከሀገራት ጋር የምታደርጋቸው የንግድ እና ሌሎች ግንኙነቶች የሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ ቀመሮችን ግምት ውስጥ የማያስገባ በመሆኑ፣ በአብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ዘንድ እንደ ዋና አጋር እየታየች ትገኛለች።
በዚህ መስመር የአብዛኞቹን ታዳጊ ሀገራት ኢኮኖሚ ለመቆጣጠር መቻሏም፣ ለም ዕራባውያኑ በተለይም ለዩናይትድ ስቴትስ ራስ ምታት ከሆነ ሰነባብቷል።