የዓባይ ግድብ ተፅዕኖ እንዲያጠኑ የተመረጡ ኩባንያዎች ጥናቱን ማራዘማቸው ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 7 ፥ 2008)

በመገንባት ላይ ያለው የአባይ ግድብ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ተፅዕኖ እንዲያጠኑ የተመረጡ ሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች በተያዘው ወር ይጀምሩታል ተብሎ የነበረው ጥናት መራዘሙ ተገለጠ።

ኢትዮጵያና ግብዕ ከኩባንያዎች ጋር ሊያደርጉት የነበረው የኮንትራት ስምምነት በተለያዩ ነጥቦች ላይ አለመግባባት በመፈጠሩ ምክንያት ጥናቱ እንዲዘገይ መደረጉን የግብፅ ባለስልጣናት ረቡዕ አስታውቀዋል።

ከሁለቱ ሃገራት የተውጣጡ የባለሙያዎች ቡድን ይፋ ያልተደረገውን አለመግባባት ለመፍታት ምክክርን እያደረጉ ሲሆን ይኸው አለመግባባት በቀጣዩ ሁለት ሳምንታት ውስጥ እልባት ሊያገኝ እንደሚችል የግብፅ የመስኖ ልማት ሚኒስትር ሆሳም ምግሃዚ መግለጻቸውን አፍሪካን ፕሬስ ኤጀንሲ ዘግቧል። ለሁለቱ ሃገራትና በሱዳን መካከል የሚፈረመውን የኮንትራት ስምምነት አንድ የብሪታኒያ ተቋም በማዘጋጀት ላይ መሆኑም ታውቋል።

ኢትዮጵያና ግብፅ በአባይ ግድብ ዙሪያ ያላቸውን አለመግባባት ለመፍታት ከአራት አመት ያህል ድርድሮችን ሲያካሄዱ ቢቆዩም አሁንም ድረስ የመጨረሻ አለመግባባት አለመድረሳቸው ይታወቃል።

ሁለቱ የፈረንሳይ ኩባንያዎች ዘጠኝ ወራቶችን ይፈጃል ለተባለው ጥናት አምስት ሚሊዮን ዩሮ የሚከፈላቸው ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ውጪውን እንደሚሸፍኑም ተገልጿል።

በሁለቱ ሃገራት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የግብፅ ኮፕቲክ ቤተ-ክርስቲያን አዲስ የውይይት መድረክን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር እንመምታካሄድ ረቡዕ ይፋ አድርጓል።

ይሁንና፣ ከኢትዮጵያ በኩል ይካሄዳል ስለተባለው የሃይማኖት ተቋማት ውይይት የተሰጠ ምላሽ የለም።