ጥር ፳፭ (ሃያ አምስት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በዋንኛነት በኦሮሚያና እና በአማራ ክልሎች ባለፈው ዓመት የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ አመጽ ተከትሎ በኢትዮጵያዊያን 2009 ግማሽ የበጀት ዓመት ከማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተገኘው የኤክስፖርት ገቢ እያሽቆለቆለ ነው።
ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንዳመለከተው ከሐምሌ 1 ቀን 2008 እስከ ታህሳስ 30/2009 ዓ.ም ባሉት ስድስት ወራት ከማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ 349 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም ማግኘት የተቻለው 199 ሚሊየን ዶላር ወይንም 57 በመቶ ያህል ብቻ ነው፡፡ በተለይ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣የጨርቃጨርቅና አልባሳት እንዲሁም ሥጋና ወተት ምርት አነስተኛ አፈጻጸም ታይቶባቸዋል፡፡
ለኤክስፖርት ምርት ማሽቆልቆል ከተሰጡት ምክንያቶች መካከል በኢንቨስትመንት ሂደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች በወቅቱ ወደማምረት ሥራ አለመሸጋገር አንዱ ምክንያት ነው፡፡ መረጃው እንደሚለው «የፕሮጀክት ሒደታቸው አጠናቀው እና ኤክስፖርት ያደርጋሉ ተብለው በዕቅድ ተይዘው የነበሩ ፕሮጀክቶች በልዩ ልዩ ምክንያቶች እና በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ችግር ምክንያት በዕቅዳቸው መሰረት ኤክስፖርት ባለማድረጋቸው ለአፈጻጸሙ ማነስ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡» ሆኖም ሚኒስቴሩ ምን ያህል ኢንዱስትሪዎች ወደስራ እንዳልገቡ በቁጥር አልገለጸም።
ለኤክስፖርት ገቢ መቀነስ የኣለም ገበያ መቀዛቀዝ በተጨማሪ ምክንያትነት ተጠቅሶአል፡፡ በዚህ ምክንያት በተለይ የበግና የበሬ ቆዳ ምርቶች ከፍተኛ የምርት ክምችትን ማስከተሉን ያብራራል፡፡
ከጥራ ጉድለትና የተወዳዳሪነት አቅም ማነስ፣ ከዓለም አቀፉ ገበያ መቀዛቀዝ፣ ከኢህአዴግ ኢንዶውመንት ድርጅቶች ኢ-ፍትሐዊ ውድድር ጋር ተያይዞ ኢንዱስትሪዎቹ ከግማሽ አቅማቸው በታች ለማምረት የተገደዱበት ሁኔታ መኖሩም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በ2009 ሩብ የበጀት ዓመት ከውጭ ንግድ የተገኘው ገቢ ከዕቅዱ ብቻ ሳይሆን ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር እንኳን ሲነጻጸር አሽቆልቁሎ ተገኝቷል፡፡ ከንግድ ሚኒስቴር ባገኘነው መረጃ መሠረት በሩብ ዓመቱ 1 ቢሊየን ዶላር ከውጭ ንግድ ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ ማሳካት የተቻለው 640 ሚሊየን ዶላር ብቻ ነው፡፡
ይህ ገቢ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ8 በመቶ ያነሰ ነው፡፡ በዚሁ ወቅት ከቡና ኤክስፖርት 212 ነጥብ 56 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት የታቀደ ሲሆን ማግኘት የተቻለው ግን 181 ሚሊየን ዶላር ብቻ ነው፡፡
በየጊዜው የኤክስፖርት ገቢ እያሽቆለቆለ መምጣት ጋር ተያይዞ ሀገሪቱ በቂ የውጭ ምንዛሪ ክምችት የሌላት በመሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አልቻለም፡፡ በውጭ ምንዛሪ ስርጭት ላይ ሙስናና ብልሹ አሰራር እየታየ መሆኑን እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦችና የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶች በአዲስአበባ ገበያ ላይ እየጠፉ እና ዋጋቸውም እየናረ ነው።