ኢሳት (ጥር 1 ፥ 2009)
ኢትዮጵያ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ የባህረ-ሰላጤ ሃገራት ገንዘባቸውን በኢትዮጵያ እንዲያስቀምጡ በመደረግ ላይ መሆኑን መንግስት ሰኞ ይፋ አደረገ። በወቅታዊ የሃገሪቱ ጉዳዮች ዙሪያ ለሃገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን መግለጫን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ፣ ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ ሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ውስጥ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ላለፉት ሶስት አመታት የውጭ ምንዛሪ ግኝቷ የቀነሰው የምትልካቸው የግብርና ምርቶች መጠን ጨምሮ ባለበት ወቅት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የአለም የግብርና ምርቶች ዋጋ ከኢትዮጵያ ቁጥጥር ውጭ ነው ያሉት አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ የዋጋ መዋዠቅ በውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።
ሃገሪቱ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ ችግር ለመቅረፍ ሲባልም በአሁኑ ወቅት የባህረ ሰላጤ ሃገራት ገንዘባቸውን በኢትዮጵያ እንዲያስቀምጡ በመደረግ ላይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃገሪቱን ስምና በኢትዮጵያ ያስቀመጡትን የውጭ ምንዛሪ መጠን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
የአለም ባንክና ሌሎች አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የውጭ ንግድ ገቢዋ እያሽቆለቆለ በመምጣቱ ሳቢያ የውጭ ምንዛሪ ገቢያ በከፍተኛ መጠን መቀነሱን ሲገልፁ ቆይተዋል። የአለም ባንክ በበኩሉ ሃገሪቱ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ የፖሊሲ ማሻሻያን እንዲሁም ብር ከዶላር ጋር የመግዛት አቅም እንዲቀንስ ሃሳብ መቅረት ይታወሳል።
የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው ባንኩ በብር ምንዛሪ ላይ ያቀረበው ሃሳብ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ሲሉ እንደማይቀበሉት ምላሽን ሰጥተዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የተከሰተውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ተከትሎ የውጭ ባለሃብቶች የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት እስከ ስድስት ወር ለመጠበቅ መገደዳቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከአመታዊ አጠቃላይ ምርቷ 40 በመቶውን ለኢንቨስትመንት እንደምታውልና ሁኔታው ለውጭ ምንዛሪ እጥረቱ አስተዋጽዖ ማድረጉን አክለው አስታወቀዋል።
የምጣኔ ሃብ ባለሙያዎች በበኩላቸው ከ36 ቢሊዮን ዶላር በላይ የደረሰው የሃገሪቱ የብድር መጠን በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫናን ማሳደሩን ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።