ኢሳት (የካቲት 8 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች ሲካሄድ የቆየውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የሃገሪቱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ባለፉት ስድስት ወራቶች ብቻ በአምስት በመቶ መቀነሱን አንድ አለም አቀፍ የፋይናንስ መጽሄት ረቡዕ ዘገበ።
ለአንድ አመት ያህል በኦሮሚያ ክልል የዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ያስነበበው ፊን-24 የተሰኘው መጽሄት በግማሽ አመቱ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ኢንቨስትመንት ለማግኘት ታቅዶ እቅዱ ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ጉድለት ማሳየቱን አመልክቷል።
በተያዘው አመት መንግስት ወደ 3.5 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ከአለም አቀፍ ንግድ ለማግኘት የያዘው እቅድም ሊሳካ እንደማይችል መጽሄቱ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሃላፊ የሆኑት አቶ ፍጹም አረጋን ዋቢ በማድረግ አስነብቧል።
በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ሲካሄዱ የቆዩ ህዝባዊ ተቃውሞዎች በኢትዮጵያ የውጭ ቀጥተኛ ተፅዕኖን እያሳደረ እንደሚገኝ ያወሳው ፊን-24 መጽሄት የሃገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት በተያዘው አመት በ7.5 በመቶ ሊያድግ እንደሚችል የአለም አቀፉን ሞኒተሪ ፈንድ መረጃ ዋቢ በማድረግ አቅርቧል።
የመንግስት ባለስጣናት የሃገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት በተያዘው አመት በሁለት አሃዝ ሊያድግ ይችላል ሲሉ በቅርቡ ትንበያን አስቀምጠው የነበረ ቢሆንም፣ አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ዕድገቱ ከሁለት አህዝ በታች ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ ላይ ናቸው።
ህዝባዊ ተቃውሞውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ውጭ ንግድ መቀነስን አስመዝግቦ የነበረ ሲሆን፣ ከቱሪዝም ዘርፍም በ10 ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር የገቢ ቅናሽ መታየቱን የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፣ አንድ የኔዘርላንድ እና ሌላ ሃገር በቀል ኩባንያዎች መንግስት በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ሲካሄድ በቆየው ህዝባዊ አመፅ ለደረሰብን ጉዳት መንግስት ካሳ ለመስጠት የገባውን ቃል አላከበረም ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት አቤቱታን አቀረቡ።
በኔዘርላንድ ባለሃብት የተቋቋመው አፍሪካ ጁስ በተቃውሞ ለደረሰበት በሚሊዮን የሚቆጠር የንብረት ጉዳት መንግስት ካሳ እንደሚሰጥ ቃል ቢገባም ካሳው ሊከፈለው እንዳልቻለ የኩባንያው ሃላፊዎች ገልጸዋል።
የመንግስት ባለስልጣናት ወደ 20 በሚጠጉ ኩባንያዎች ላይ ደርሶ በነበረው ጥቃት ወደ 100 ሚልዮን ብር የሚጠጋ ጉዳት መድረሱን በመግለጽ ለድርጅቶቹ ካሳ እንደሚከፍል ቃል መግባታቸው ይታወሳል።
ከኔዘርላንድ ኩባንያ በተጨማሪ የሃዋሳ የግብርና ልማት ድርጅት በተመሳሳይ መልኩ ከመንግስት የተገባለት የካሳ ክፍያ ተግባራዊ አለመደረጉን አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አቤቱታ ማቅረቡን ለመረዳት ተችሏል።
በሃገሪቱ ሊካሄድ የነበረውን ተቃውሞ ምክንያት በማድረግ የኢንቨስትመንት ስራቸውን ጥለው የወጡ ኩባንያዎች ባይኖሩም አብዛኞቹ የውጭ ተቋማት ነገሮችን በትዕግስት እየተጠባቁ እንደሚገኝ የፋይናንስ መጽሄቱ በዘገባው አስፍሯል።