ጥር ፲፰ (አሥራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የእር ሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው በውጪ ምንዛሪ ችግር ምክንያት ለእርሻ ግብአት የሚውል ማዳበሪያ በበቂ መጠን መግዛት እንዳልተቻለ ለፖርላማው ገልጸዋል፤፡
ለመስኖና እና ለበልግ እርሻ ማዳበሪያ በወቅቱ ለአርሶአደሩ እንዲቀርብ ለማድረግ 832 ሺህ 400 ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ለመግዛት ታቅዶ በውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር ጋር ተያይዞ በመተማመኛ ሰነድ (ሌተር ኦፍ ክሬዲት) አከፋፈት ላይ መዘግየት በመፈጠሩ መግዛት የተቻለው 19 ሺህ 315 ሜትሪክ ቶን ብቻ ነው። ሚኒስትሩ እንዳሉት እንደእቅዳቸው ቢሆን ኖሮ እስካሁን ወደሀገር ውስጥ መግባት የነበረበት 200 ሺህ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ነበር።
የማዳበሪያ ግዥው በመንግስት ቅድሚያ ማግኘት አለመቻሉ የዝናብ መሻሻል የሚያሳዩ አካባቢዎች አርሶአደሩ የእርሻ ግብአቶችን ተጠቅሞ በቂ ምርት እንዳያገኝ እንቅፋት በመሆን የድርቁን ችግር ያባብሳል በሚል በብዙዎች ዘንድ ስጋትን አሳድሮአል።
የምንዛሬ እጥረቱ በመድሃኒቶች ዋጋ ላይም ጭማሪ እንዲታይ አድርጓል። መንግስት የምንዛሬ እጥረት የለም በማለት በተደጋጋሚ ማስተባበያ ይሰጣል። ይሁን እንጅ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ በአጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴው ላይ ተጽእኖ እያሳረፈ መምጣቱን ነጋዴዎች ይናገራሉ።