ኢሳት (ሚያዚያ 19 ፥ 2008)
የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኙ ታስበው በመንግስት ልዩ የማበረታቻ ድጋፍ ሲደረግላቸው የቆዩ ከ30 በላይ ኩባንያዎች በየወሩ ስድስት ሚሊዮን ዶላር እንዲያስገኙ ቢጠበቅባቸውም ከ90 ሺ ዶላር በታች ማስመዝገባቸው ተገለጠ።
በጉዳዩ ቅሬታ የተሰማቸው የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው ድርጅቶቹ ሲደረግላቸው የቆየ ልዩ ልዩ ድጋፍ ተቋርጦ በኩባንያዎቹ ላይ ምርመራ እንደሚካሄድ አሳስበዋል።
እነዚሁ በብረታ-ብረትና በኤሌክትሮኒክስ ማምረት ተግባር ላይ ተሰማርተው የሚገኙት ድርጅቶች ለምርት ግብዓት የሚሆናቸውን ጥሬ እቃ ያለቀረጥ ወደሃገር ውስጥ እንዲያስገቡና ሌሎችም ድጋፎች ሲደረጉላቸው መቆየቱን የብረታብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ይፋ አድርጓል።
ይሁንና መንግስት ከኩባንያዎቹ አገኘዋለሁ ብሎ ሲጠብቅ የነበረ የውጭ ምንዛሪ አለመገኘቱንና ድርጊቱ በሃገሪቱ የፋይናንስ ስርዓት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳሰሩም ተገልጿል።
ወደ 35 የሚደርሱ ኩባንያዎች በየወሩ በአማካይ ስድስት ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ያስገኛሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ ከ90ሺ ዶላር በታች ማስገባታቸውን የኢንስቲትዩቱ ባለስልጣናት ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
የገበያ እጦት እንዳጋጠማቸው አስታውቀዋል የተባሉት ድርጅቶች ምርታቸውን ለሃገር ውስጥ ገበያ በማቅረባቸው ምክንያት መንግስት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንዳጣ መንግስታዊው ኢንስቲትዩት አመልክቷል።
የኢትዮጵያ የውጭ ገቢ ንግድ እያሽቆለቆለ መምጣትን ተከትሎ መንግስት በዘርፉ በተሰማሩ የንግድ ተቋማት ላይ ምርመራን እያካሄደ ሲሆን ከተለያዩ የእርሻ ስራዎች ለውጭ ባለሃብቶች የተሰጡ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችም በመንግስት ላይ ኪሳራ መስከተላቸው ይታወቃል።
በተለይ የውጭ ምንዛሪን ያስገኛሉ ተብሎ ልዩ ድጋፍ ሲደረግላቸው የቆዩ ኩባንያዎች ሊያመጡ ከታሰበው ጥቅም ይልቅ ኣያደረሱ ያለው ኪሳራ ከፍተኛ መሆኑንም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተለያዩ ክልሎች ለውጭ ኩባንያዎች በልዩ ድጋፍ ሲሰጥ በቆየው ሰፋፊ የእርሻ መሬት ላይ በብድር የተሰጠ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የገባበት አለመታወቁን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ለጥጥ ምርት በተሰጠ የእርሻ መሬት ላይ ተመሳሳይ ኪሳራ ያጋጠመ ሲሆን፣ ሃገሪቱ የጥጥ ምርትን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የያዘችው እቅድ ሳይሳካ መቅረቱንም የመንግስት ባለስልጣናት ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርገዋል።