የውጭ ምንዛሪ ያመጣሉ ተብለው ድጋፍ ሲደረግላቸው የነበሩ 19 ኩባንያዎች በዚህ አመት ምንም አለማምረታቸው ታወቀ

ኢሳት (ግንቦት 8 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ ምርትን ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ የተለያዩ ድጋፎች ሲደረጉላቸው ከቆዩ 60 ኩባንያዎች መካከል 19ኙ በተያዘው በጀት አመት ምንም ምርት ሳይልኩ መቅረታቸው ተገለጠ።

ኩባንያዎቹ ሲጠበቅባቸው የነበረን ምርት ከውጭ ገበያ ባለማቅረባቸው ምክንያትም መንግስት በበጀት አመቱ ሊያገኝ ካሰበው የውጭ ምንዛሪ ውስጥ የ45 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ መመዝገቡን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ይሁንና 19 የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች የተለያዩ ድጋፎች ሲደረግላቸው ቢሆንም አንድም ዶላር ገቢ ሳያስገኙ መቅረታቸውን መንግስታዊ ተቋም አመልክቷል።

የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎቹ ያስገኛሉ ተብሎ ይጠበቅባቸው የነበረን የውጭ ምንዛሬ ባለማስገኘታቸውም በሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸው ታውቋል።

የንግድ ሚኒስቴር በበኩሉ ከጨርቃ ጨርቅ ምርት ይገኝ ለነበረው ገቢ ማሽቆልቆል ፋብሪካዎቹን ተጠያቂ በማድረግ ኩባንያዎቹ የገበያ አማራጮችን አላስፋፉም ሲል ቅሬታ እንዳቀረበባቸውም ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

መንግስት ለሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛሉ ብሎ ላሰባቸው በርካታ ኩባንያዎች ድጋፍን ሲያደርግ ቢቆይም፣ ከተቋማቱ ግን በቂ ገቢ አለመገኘቱንና ድርጊቱ ኪሳራን እያስከተለ እንደሚገኝ የመንግስት ባለስልጣናት በመግለጽ ላይ ናቸው።

ይህንንም ተከትሎ ከቀረጥ ነጻ እድል ከተሰጣቸው ኩባንያዎች ታክስን መልሶ ለማስከፈል መንግስት በቅርቡ አዲስ መመሪያን ማስተዋወቁ ይታወሳል።

ይሁንና፣ በውጭ ንግድ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ያጋጠሟቸው ችግሮች በቂ ትኩረት ሳይሰጣቸው ታክስን መልሶ ለማስከፈል የተወሰደው ውሳኔ አግባብ አለመሆኑን በመግለጽ ላይ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።

ሃገሪቱ አጋጥሟት ያለው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና እድገትን እያሳየ ያለው የዋጋ ግሽበት በሃገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮ እንደሚገኝም የተለያዩ አካላት ሲገልጹ ቆይተዋል።