የውጭ ምንዛሪ እጥረት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ፈጥሯል

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 10/2010)

የወጭ ንግድ ሚዛን መዛባትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ደንቃራና ቀውስ መፍጠሩን አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት/አይ ኤም ኤፍ/ አስታወቀ።

የአይ ኤም ኤፍ የቦርድ ዳይሬክተሮች በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ባካሄዱት ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያን በተመለከተ ባካሄዱት ምክክር የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለአንድ አመት ከ8 ወራት ብቻ የሚበቃ ነው።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመስቀለኛ መንገድ ላይ የቆመ እንዲሆን ያደረገውም ግሽበትን መቆጣጠር አለመቻሏ እንደሆነም አይ ኤም ኤፍ አስታውቋል።

የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት/አይ ኤም ኤፍ/ የልኡካን ቡድን ባለፈው መስከረም ወር ላይ በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርጎ አንድ የቅኝት ሪፖርት አቅርቦ ነበር።

የልኡካን ቡድኑ ሃላፊ ጁልዬ ኤስኮላኖ ያቀረቡትን የቅኝት ሪፖርት መነሻ በማድረግም የአይ ኤም ኤፍ የቦርድ ዳይሬክተሮች ጉዳዩን መርምረው የማጠቃለያ ግምገማ አድርገዋል።

በዚሁም መሰረት በኢትዮጵያ የወጭ ንግድ መዛባትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ደንቃራና ቀውስ ማስከተሉን የአይ ኤም ኤፍ ቦርድ አስታውቋል።

እንደ ቦርድ አመራሩ ገለጻ ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2016/17 የነበራት የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ብቻ ነበር።

ይህም ሸቀጦችንና ምርቶችን ለማስገባት ለአንድ አመት ከ8 ወራት ጊዜ ብቻ የሚበቃ እንደሆነ ነው የገለጸው።

ኢትዮጵያ ያላት የበጀት ጉድለትም በ3 ነጥብ 5 በመቶ መጨመሩንም አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት /አይ ኤም ኤፍ/ አስታውቋል።

እናም በኢትዮጵያ ያለው መንግስት የወጭ ንግድ ሚዛን መዛባቱን ለመከላከል የውጭ ብድር ማቆም እንዳለበት ነው የመከረው።

ይህን ብቻ አይደለም ኢትዮጵያ የፖሊሲ ርምጃና ለውጥ ማድረግ እንደሚጠበቅባትም አሳስቧል።

ሀገሪቱ የገቢ ንግዷን በመቀነስና የወጭ ምርቷን በማብዛት ርምጃ ካልወሰደች በኢኮኖሚዋ ላይ ደንቃራና ቀውስ እንደሚያመጣ ጠቁሟል።

ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚም ትኩረት መሰጠት አለበት ብሏል።

በመንግስት ስር ያሉ ከፍተኛ የንግድ ተቋማትም ወደ ግል መዞር አለባቸው ነው ያለው።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሚናም ብድር አሰጣጥን በተመለከተ ከጠቃሚነቱ ይልቅ አሰራሩ የተዛባ መሆኑን አይ ኤም ኤፍ ገልጿል።

በኢትዮጵያ 8 ነጥብ 5 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት እንደሚኖር አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ተንብይዋል።

ሪፖርቱ በርካታ ችግሮችን ስለኢትዮጵያ ቢተነትንም የሀገሪቱ የመንግስት መገናኛ ብዙሃንና የህወሃት ንብረት የሆነው ሬዲዮ ፋና አይ ኤም ኤፍ ኢትዮጵያ በእድገት ላይ እንደምትገኝ መግለጹን እየተነተኑ ይገኛሉ።