የውጭ ምንዛሪ አገልግሎትን ያለህጋዊ ፈቃድ ይሰጣሉ በተባሉ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ተባለ

ኢሳት (ጥቅምት 24 ፥ 2009)

የአዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች የውጭ ምንዛሪ አገልግሎትን ያለህጋዊ ፈቃድ ይሰጣሉ በተባሉ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑን ነዋሪዎች አስታወቁ።

የጸጥታ ሃይሎች የቤት ለቤት ፍተሻን ጭምር እያካሄዱ ባለው በዚሁ ዘመቻ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከተቋማቱና ከግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር መዋሉን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጠቀም ያልተጠበቀ ፍተሻን እያካሄዱ ያሉ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ፍተሻቸውን በሚያካሄዱበት ጊዜ ከውጭ ሃገር የተላከላችሁ ገንዘብ አለ ወይ የሚል ጥያቄን እንደሚያቀርቡም ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ህገወጥ የውጭ ምንዛሬ አገልግሎት ይካሄድባቸዋል በተባሉ አካባቢዎች የደንብ ልብስን ያልለበሱ የደህንነት ሃይሎች ክትትል በማካሄድ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር እያዋሉ እንደሆነም ታውቋል።

የጸጥታ ሃይሎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተሰጣቸው ስልጣን ግልጽ አልሆነልንም ሲሉ የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ግንኙነት በሌላቸው ጉዳዮች ላይ ማብራሪያን እንዲሰጡ ግፊት እየተደረገባቸው መሆኑን ይገልጻሉ።

ሃገሪቱ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ተከትሎ የብሄራዊ ባንክ ህገወጥ የገንዘብ ልውውጥ በሚያካሄዱ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ እርምጃ እንዲወስድ ከሶስት አመት በፊት መመሪያ ማውጣቱ ይታወሳል።

ይሁንና አዲሱ መመሪያ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጠቀም በውጭ ሃገር የገንዘብ ዝውውር ላይ ሰፊ ዘመቻ ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ተነግሯል።

የአለም ባንክን ጨምሮ በርካታ አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የኢትዮጵያ መንግስት አጋጥሞት ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት መቅረፍ የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለበት ሲያሳስቡ ቆይተዋል።

ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ መንግስት ያጋጠመውን የውጭ ንግድ መቀዝቀዝና የአለም አቀፉ ብድር እዳ መጨመር ተከትሎ በመንግስት የፋይናንስ አቅም ላይ ጫና ማሳደሩን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ባለፈው አመት በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ በሃገሪቱ የውጭ ንግድ ገቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ ታውቋል።