ኢሳት (ሚያዚያ 3 ፥ 2009)
የብሄራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የሚፈልጉ የሃገር ውስጥ ኩባንያዎች ሌተር ኦፍ ክሬዲት (LC) ለመክፈት ያስቀመጠውን የ30 በመቶ መጠን ወደ 100 ፐርሰንት ከፍ አደረገ።
ባንኩ የወሰደውን ይህንኑ ዕርምጃ ተከትሎ አስመጪ ነጋዴዎች በግል ባንክ ያስቀመጡትን ገንዘብ በማውጣት ወደ ብሄራዊ ባንክ ለማስገባት መገደዳቸውን አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በበኩላቸው ዕርምጃው የግል ባንኮች የገንዘብ እጥረት እንዲያጋጥማቸው በማድረግ የማዳበር አቅማቸውን ሊጎዳ እንደሚችል ገልጸዋል።
ብሄራዊ ባንክ ተግባራዊ ያደረገውን ይህንኑ አዲስ አሰራር ተከትሎ የብሄራዊ ንግድ ባንክ ለአስር ወር ያህል ዘግይቶ የቆየን የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ ማስተናገድ መጀመሩ ታውቋል።
ባንኩ ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር አስመጪ ነጋዴዎች ሌተር ኦፍ ክሬዲት ለመክፈት ከሚፈልጉት ገንዘብ ውስጥ 30 በመቶውን እንዲያስይዙ የሚጠይቅ የነበረ ሲሆን፣ ይህንኑ ተቀማጭ ገንዘብ ወደ 100 ፐርሰንት ማሳደጉን ጋዜጣው በዘገባው አመልክቷል። በማምረቻው ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች የውጭ ምንዛሪውን ለማግኘት ቅድሚያ እድል እንደተሰጣቸው ታውቋል።
ይሁንና ብሄራዊ ባንክ የወሰደው አዲስ እርምጃ ከፍተኛ መጠን ገንዘብ ከሁሉም የግል ባንኮች እንዲወጣ ማድረጉንና ድርጊቱን የባንኮቹን ህልውና እንደሚፈታተን ስማቸውን መግለፅ ያልፈልጉ የባንክ ባለሙያዎች አስረድተዋል።
የህብረት ባንክ የቦርድ ጸሃፊ የሆኑት አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ የግል ባንኮች እያጋጠማቸው ያለው የተቀማጭ ገንዘብ መቀነስ የባንኮቹን የማዳበር አቅም የሚገድል ነው ሲሉ ለጋዜጣው ገልጸዋል።
ዕርምጃው በስራ ላይ ያሉትንም አሁን አዲስ የሚቋቋሙ ባንኮች በፅኑ የሚጎዳ እንደሆነም የባንክ ባለሙያው አክለው ተናግረዋል።
የግል ባለሃብቶች ከመንግስት ባንክ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት በሚል ካለፈው ሁለት ሳምታት ጀምሮ ገንዘባቸውን ከግል ባንክ በማስወጣት ላይ ሲሆኑ ባንኮቹ ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር ሊያጡ እንደሚችል የባንክ ባለሙያዎች አስታውቋል።
ከማዕከላዊ ባንክ ተገኝቷል የተባለን የውጭ ምንዛሪ ተከትሎ ንግድ ባንክ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ የውጭ ምንዛሪን ለአስመጪ ነጋዴዎች ለመስጠት መወሰኑን ለመረዳት ተችሏል። ይሁንና የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የብሄራዊ ባንክ ከመንግስት በኩል እየተደረገበት ያለው ልዩ ድጋፍ የግል ባንኮች ተወዳደሪነት እንዲሁም የገንዘብ ተቀማጭ አቅማቸውን እንደሚጎዳ አሳስበዋል።
ባለፈው አመት ኢትዮጵያ ለገቢ ንግድ ወደ 16 ቢሊዮን ዶላር አካባቢን ወጪ ያደረገች ሲሆን፣ ከውጭ ንግድ ያገኘችው ገንዘብ ግን ሶስት ቢሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
የገቢና የውጭ ንግድ ባለመመጣጠኑ ምክንያት ሃገሪቱ ላለፉት አመታት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ውስጥ መቆየቷ የሚታወስ ሲሆን፣ የአለም ባንክ በበኩሉ ኢትዮጵያ ችግሩን ለመቅረፍ የፖሊሲ ማሻሻያ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባት ያሳስባል።
የአለም ባንክ እንዲሁም ሌሎች የፋይንናንስ ተቋማት መንግስት በተለያዩ ጊዜያት በግል ባንኮች ላይ ተግባራዊ የሚያደርገው አስገዳጅ መመሪያ የባንኮቹን ህልውና የሚጎዳ እንደሆነ ሲያሳስቡ ቆይተዋል።
የብሄራዊ ባንክ በቅርቡ የግል ባንኮች ተከፋይ የሆነ ተቀማጭ ካፒታላቸውን ከፍ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ መመሪያ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን መግለፁ ይታወሳል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ዕርምጃው የግል ባንኮች እንዲዋሃዱ የሚያደርግ እንደሆነና፣ አዲስ የሚቋቋሙ ባንኮች ተስፋ የሚያስቆርጥ እንደሆነ ገልጸዋል።