(ኢሳት ዜና –ነሐሴ 1/2009)የውጭ ሀገር ምንዛሪ ይዛችሁ ተንቀሳቅሳችኋል የተባሉ የውጭ ሀገር ዜጎችና ኢትዮጵያውያን በሳምንቱ መጨረሻ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተሰማ።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት የታሰሩት ግለሰቦች በአለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት ውስጥ በመስራት ላይ የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል።
የውጭ ሀገር ምንዛሪ ይዛችሁ በሚል በተለይ በውጭ ሀገር ዜጎች ላይ ተነጣጥሯል በተባለው በዚህ የእስራት ዘመቻ በአለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ የውጭ ዜጎችና ቤተሰቦቻቸው ጭምር ሰለባ መሆናቸው ተመልክቷል።
ግለሰቦቹ ከተለያዩ አካባቢዎች ከመንገድ ላይ ጭምር መያዛቸውን ነው ምንጮቹ የገለጹት።
ከያዙት የውጭ ምንዛሪ ጀርባ ማን አለ ወይንም ገንዘቡ የየትኛው ባለስልጣን ወይንም ነጋዴ ነው የሚል ጥያቄ እንደቀረበላቸውም ታውቋል።
መንግስት ወደዚህ ዘመቻ የገባው በአንድ በኩል የከፈተው የጸረ ሙስና አካል በማድረግ ይሆናል ሲሉ አንዳንዶች ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ሀገሪቱ የገባችበት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ቀውስ ዋናው ምክንያት እንደሆነም እየተነገረ ይገኛል።
ከመንገድና ከተለያዩ ስፍራዎች ተይዘው የታሰሩት እነዚህ የአለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት ሰራተኞች ሰኞ ነሀሴ 1/2009 ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ቢገለጽም ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ችሎት ስለመቅረባቸው የታወቀ ነገር የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለም መንግስት በገጠመው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ቀውስ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም በልዩ ልዩ አለምአቀፍና አሕጉራዊ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ግለሰቦች ለመንግስት የሚከፍሉትን ግብር የመብራት፣ የስልክ፣ የውሃና ልዩ ልዩ ወጭዎች በውጭ ምንዛሪ እንዲሞሉ ይህም በፓስፖርት ወይንም በቪዛ ካርድ እንዲፈጸም መንግስት አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑንም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።