የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በያዝነው 2007 በጀት ዓመት 10 ወራት ከኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርትና ከሀገር ውስጥ ሽያጭ ከፍተኛ ገቢ ማግኘቱን ይፋ አደረገ፡፡

ግንቦት ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአዲስ አበባና በክልሎች የኤሌክትሪክ ኃይል በየዕለቱ እየተቆራረጠ ምርታማነት ባሽቆለቆለበት በዚህ ወቅት ሚኒስቴሩ ለጎረቤት ሀገራት ባለፉት 10 ወራት ብቻ
606 ነጥብ 5 ሚሊየን ኪ.ዋ. የኤሌክትሪክ ኢነርጂ በመሸጥ ዳጎስ ያለ ገቢ ማግኘቱን ይፋ አድርጓል፡፡
በሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግር ከጊዜ ወደጊዜ ተባበሶ በቀን በአማካይ አንድ ጊዜ የሚጠፋበትና ምርትና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መደበኛ ሥራቸው የተስተጓጎለበት ሁኔታ ቢኖርም ሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤት ሀገራት
እየሸጠች ነው ፡፡ በያዝነው በጀት ዓመት ከኢነርጂ ሽያጭ ብቻ 2 ነጥብ 87 ቢሊየን ብር ወይም ከ143 ሚሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱን አቶ አለማየሁ ተገኑ ሰሞኑን ለፓርላማው ካቀረቡት ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡
በኤሌክትሪክ እጥረት ምክንያት አምራች ኢንዱስትሪዎች ሥራቸውን ለማከናወን የተቸገሩ ሲሆን ለውጪ ገበያ የሚሰሩ ፋብሪካዎች በገቡት ውል መሰረት ምርት ለማቅረብ ባለመቻላቸው ለኪሳራ እየተዳረጉ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት እንደኬንያ እና ጅቡቲ ላሉ ሀገራት ኤሌክትሪክ ኃይል የማቀርበው ከተረፈኝ እንጂ ካለው ቀንሼ አይደለም ቢልም በተግባር ግን የሀገር ውስጥ አቅርቦትን በማስተጓጎል ለውጪ ገበያ የማቅረብ፣ የሀገርን ጥቅም ያላገናዘበ እርምጃ
መሆኑ እየታየ ነው፡፡
ፓርላማው የኃይል መቆራረጥ ችግርን ለመቅረፍ ምን እየተሰራ እንደሆነ ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም ሚኒስትሩ እየተሻሻለ ነው በሚል ከእውነታው ጋር የተቃረነ ድፍን ያለ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡