ሐምሌ ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ወርሃዊ የዋጋ መረጃው በሰኔ ወር 2007 ዓ.ም የሸቀጦች ዋጋ ካለፈው ጋር ሲነጻጸር መጨመሩን ይፋ አደረገ፡፡ በኤጀንሲው መረጃ መሰረት በግንቦት ወር 9 ነጥብ 4 በመቶ የነበረው የዋጋ ግሽበት በሰኔ ወር ወደ 10 ነጥብ 4 በመቶ ከፍ ብሏል። በዚህም ምክንያት ኢህአዴግ መራሹ መንግስት የዋጋ ግሽበትን ወደአንድ አሃዝ አውርጃለሁ በማለት ባለፉት ወራት ሲሰራ የነበረውን ፕሮፖጋንዳ የኤጀንሲው መረጃ ውድቅ አድርጎታል፡፡
በሰኔ ወር በከፍተኛ ደረጃ ንረት ከታየባቸው ሸቀጦች መካከል የምግብና ምግብ ነክ ውጤቶች የመጀመሪያውን ረድፍ ይዘዋል፡፡ በምግብና ምግብ ነክ ምርቶች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ባለፈው ወር ከነበረበት 10 ነጥብ 1 በመቶ ወደ 12 ነጥብ 4 በመቶ በከፍተኛ ደረጃ ያሻቀበ ሲሆን በተለይም በስጋ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ከፍተኛ መሆኑን የኤጀንሲው ጥናት ጠቁሟል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በተለይም በቋሚነት እየተቆራረጠ ከሚገኘው የመብራት ኃይል አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ፋብሪካዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በማሳረፉ እንደሲሚንቶ ያሉ የሀገር ውስጥ ምርቶች ከ230 ብር ዋጋ ወደ 450 ብር በኩንታል ንረት ያሳዩ ሲሆን ፣ በሀገር ውስጥ የሚመረት የምግብ ዘይት ፣ አብዛኛው መካከለኛና ደሃ ህብረተሰብ አዘውትሮ የሚመገበው የምስር ምርት፣ድንችና ካሮት በአስደንጋጭ ሁኔታ ዋጋቸው ጨምሯል።
የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሶፊያን አህመድ በቅርቡ የ2008 በጀትን ለፓርላማ ሲያቀርቡ ሀገሪቱ ጥብቅ የበጀትና የገንዘብ ፖሊሲዎችን በመተግበርዋ የዋጋ ዕድገት በአንድ አሃዝ እንዲወሰን ማድረግ ተችሏል በሚል እንደከፍተኛ ስኬት መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡