መጋቢት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የጤፍ የችርቻሮ ዋጋ የጨመረባቸው ዋነኛ ምክንያቶች በኮንትሮባንድ ከሀገር እየወጣ በመሆኑና አርሶ አደሩም በአብዛኛው በአፈር ጥበቃ ሥራ ከመሰማራቱ ጋር በተያያዘ ምርቱን ወደ ገበያ ይዞ በመውጣቱ መሆኑን የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓሊ ሲራጅ መግለጣቸውን ሰንደቅ ዘግቧል።
አቶ ዓሊ የጤፍ ምርት ዋጋ እንዲቀንስ መንግስት በአካባቢና አፈር ጥበቃ ላይ የተሰማራው ገበሬ ምርቱን ወደ ገበያ ይዞ እንዲወጣ ሰፊ ቅስቀሳ እያደረገ መሆኑን እንዲሁም በተለይ በጋምቤላ በኩል የጤፍ ምርት በኮንትሮባንድ ከሀገር እየወጣ ያለበት ሁኔታ በመታየቱ ችግሩን ለመቆጣጠር በጐረቤት ሀገራት ዋና ዋና መውጫዎች ላይ ቁጥጥር የማድረጉ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።
መንግስት ምንም እንኳን የጤፍ ምርት በቅርቡ የዋጋ መጨመር ሁኔታ ቢታይበትም ስንዴን ከውጪ አስመጥቶ በድጐማ በማሰራጨት የገበያው ሁኔታ እንዲረጋጋ ሰፊ ጥረት እያደረገ መሆኑን 8 ሚሊዮን ኩንታል መግዛቱን ጋዜጣው ዘግቧል።
ሚኒሰትሩ የሰጡት መልስ በአገሪቱ የሚታየውን መሰረታዊ የአቅርቦት ችግር ለመሸፋፋን ተብሎ የታቀደ ነው የሚሉ አንድ ባለሙያ አስተያየታቸውን ለኢሳት ገልጠዋል። አርሶ አደሩ የአካባቢ አፈር ጥበቃ በግዳጅ እንዲሰራ የሚደረገው በሳምንት ውስጥ የተወሰኑ ቀናት ነው። ቅዳሜ ቀን ደግሞ በየትኛውም አካባቢ ስራ የሚባል ነገር የለም፤ ታዲያ አርሶ አደሩ በአፈር ጥበቃ ላይ በመሰማራቱ ጤፍ ተወደደ የሚለው ምክንያት ተቀባይነት የለውም ይላሉ።
ገበሬው ምርቱ ቢኖረው በማንኛውም ጊዜ ወደ ገበያ ለማውጣት አያስቸግረውም ምክንያቱም እርሱም ለመኖር ከከተማ የተወሰኑ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን መግዛት ግድ ይለዋል፣ ስለዚህ መንግስት ህብረተሰቡን ለማታለል የሚሰጠው መግለጫ የሚያሳዝን መሆኑን አክለው ገልጠዋል።
የካቲትና መጋቢት የጤፍ ዋጋ የሚረክስበት ወቅት ቢሆንም ዘንድሮ ግን ከዚህ ቀደም ባልታየ መልኩ ጭማሪ አሳይቷል። በአዲስ አበባ ነጭ ጤፍ 1700 ብር ድረስ በመሸጥ ላይ ሲሆን አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ በቀር ዋጋው 2 ሺ ብር በኩንታል ሊገባ ይችላል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ ሶፍያን አህመድ የመስሪያ ቤታቸውን የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ዛሬ ለፓርላማ ሲያቀርቡ መንግስት የዋጋ ማረጋጋት ለማድረግ በዚህ ወር ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። አቶ መለስ ዜናዊ ከወር በፊት ባደረጉት ንግግር የዋጋ ንረቱን በሳምንታት ውስጥ እንቆጣጠረዋልን ብለው መናገራቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግስት የዋጋ ግሽበትን እንዲቆጣጠርና ቁጠባን እንዲያሳድግ የአለም የገንዘብ ድርጅት ማሳሰቡ ይታወሳል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide