(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 28/2010) በወህኒ ቤት የሚገኙት የዋልድባ መነኮሳት እንዲፈቱና በእስር ቤት ውስጥ የሚፈጸምባቸው በደል እንዲቆም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት ጠየቀ።
ሌሎች የፖለቲካና የሕሊና እስረኞች እየተፈቱ ባሉበት ወቅት የዋልድባ መነኮሳትን በወህኒ ቤት ውስጥ ማገትና ማጎሳቆል የሕወሃት መንግስት ለቤተክርስቲያኒቱ ያለውን ጥላቻ የሚያሳይ ነው ሲልም ሕብረቱ አመልክቷል።
“ወይባና አስኬማ የዋልድባ መነኮሳት ክብር” በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት ባወጣውና ለዋልድባ መነኮሳት አጋርነቱን በገለጸበት መግለጫው የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት የኢትዮጵያ ማህበራዊና ሃይማኖታዊ እሴቶቹን ማውደሙን ቀጥሏል ሲልም አውግዟል።
“በኦርቶዶክስና በሙስሊም ምዕመናን ዘንድ በእውቀታቸው፣በባህሪያቸውና በአርአያነታቸው የተመሰገኑ፣የተከበሩና ተአማኒነት ያላቸውን ፓትሪያርክ፣ኢማሞች፣ጳጳሳትና ሺሆች እንዲሁም የቀሳውስትን ክብር በሚነካ መልኩ በጉልበት በማስወገድ ለእስርና ለስደት ዳርጓል።”በማለት ስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ይወቅሳል።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት መግለጫ በሃይማኖት መሪዎቹ ምትክ በየመስጊዱና በየአብያተ ክርስቲያናቱ ዕውቀት የሌላቸውን ካድሬዎች በመሰግሰግ መንፈሳዊ ስፍራዎችን አርክሷል በማለት ስርአቱን ተጠያቂ አድርጓል።
የታሪክ ቅርስ የሆነውን የዋልድባ ገዳም ከማፍረስ ባሻገር መነኮሳቱን በወህኒ በማገትና በማሰቃየት እንዲሁም መንፈሳዊ ልብሳቸውን እንዲያወልቁ በማስገደድ የሚፈጸመባቸውን በደልም በዝርዝር አስቀምጧል።
እነዚህ መነኮሳት ከሌሎች የህሊና እስረኞች ተለይተው በወህኒ እንዲቀሩ መደረጉ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት መሆኑንም አመልክቷል።
በመነኮሳቱ ላይ የሚፈጸመው በደልና ስቃይ የሙስሊሙን ማህበረሰብ ያመዋል ያለው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት፣የእምነት ተቋማትም ሆነ የሃገሪቱ ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚፈታው ሕዝባዊ አመጽ ሲፋፋምና የትግራይ ነጻ አውጪ ነኝ የሚለው ቡድን ከስሩ ሲነቀል ብቻ ነው ሲል መግለጫውን ቋጭቷል።