ሰኔ ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት ገዳም አራት መነኮሳት ባለፈው ቅዳሜ በመንግስት ታጣቂዎች ተይዘው መወሰዳቸውንና ገዳሙም ከሰሜን ጎንደር ዞን በተላኩ በርካታ የፌዴራል ፖሊሶች ተከቦ እንደሚገኝ “ደጀ ሰላም” የተሰኘው ድረገጽ በዝርዝር ዘገበ።
እንደ ዜናው ዘገባ በሱባኤ ላይ የነበሩ በርካታ መነኮሳትም በፖሊሶች ዱላ ተደብድበው እንዲበተኑ መደረጋቸው ታውቋል። ከገዳሙ ከተወሰዱት አራት መነኰሳት መካከልም ሶስቱ አባ ኀይለ ኢየሱስ፣ አባ ግርማይ፣ አባ ገብረ እግዚአብሔር ተብለው የሚጠሩ ሲሆን፣ የአራተኛውን መነኩሴ ስም ግን ለጊዜው ለማወቅ አልተቻለም፡፡
የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት በገዳሙ ህልውናና ክብር ላይ በጋረጠው ስጋት ሳቢያ የሰቋር ኪዳነ ምሕረት ማኅበረ መነኰሳት ግንቦት 22 ቀን “ኑ ፣ ታቦቱን፣ ቅርሱን ተረከቡ፤ እኛ እንፈልሳለን ወይም ወደ በርሓ እንሰወራለን” የሚል ጥሪ ለምእመኑ ማስተላለፋቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎም በዓዲ አርቃይ ወረዳ ሳንቅ፣ ዛሬማ፣ ያሊ፣ የጥራይና፣ ጅሮሰ፣ ነብራና ፍድቃ የተሰኙት ቀበሌዎች ነዋሪዎች ዛሬማና ሰቋር ላይ በመሰብሰብ ተቃውሟቸውን አጠናክረው መቀጠላቸው ታውቋል።
ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ እየገለፁ ያሉ በርካታ ወጣቶችም ተይዘው እየታሰሩና ድብደባም እየፈፀመባቸው እንደሆነ የሚገልፀው የደጀሰላም ዘገባ፣ በአካባቢው እያየለ የመጣውን የምዕመናኑን ተቃውሞ ለማርገብ የክልሉን ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው ጎበዜን ጨምሮ፣ የቤተክርስቲያኗ መንበር ላይ ተቀምጠው የመንግስትን አቋም የሚያራምዱ የሃይማኖት አባቶች በተደጋጋሚ ያደረጉት ጥረት ሊሳካ እንዳልቻለ ይገልፃል።
እነዚሁ የመንግስትና የአቡነ ጳውሎስ ተወካዮች መነኮሳቱን፣ “ሃይማኖትን ሽፋን እያደረጋችኹ የፖለቲካ ዘመቻ ታደርጋላችኹ፤ የፀረ ሰላም፣ ፀረ ልማት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰለባ ኾናችኋል፤ የእነርሱን ድምፅ ነው የምታስተጋቡት፤” እያሉ በግልጽ ከመዛለፋቸውም በተጨማሪ “ብትስማሙና የሸንኮራው ልማት ቢለማ ምናለበት?” በማለት በተደጋጋሚ ለማግባባት ሞክረዋል። ሆኖም መነኰሳቱ በበኩላቸው “በልቅሶ ነው ያለነው፤ ዐፅም ወጥቶ ውኃ አይቆምም፤ ቤተ ክርስቲያን እየፈረሰ በሚለማ ልማት አንስማማም፤ ዋልድባ ቅንጣት ያህል አትነካም›፤ ይህ የሃይማኖት ጉዳይ እንጂ የፖለቲካ አይደለም” በማለት ያላቸውን አቋም በግልጽ አስረድተዋል።
የዋልድባ ገዳም የሚገኝባቸው ሦስቱ አህጉረ ስብከቶች፣ እንዲሁም የወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የገዳሙን ሕልውና እየተዳፈረ ያለውን የመንግስት ውሳኔ በመቃወም ከሌላው የቤተክርስቲያኗ ተቆርቋሪዎች ጎን ያለመቆማቸው ያሳዘነው ምእመኑ ከዘንድሮው ዓመት ጀምሮ “የነፍስ ዐሥራት በኵራት” ሲል የሚጠራውን መባዕና የሰበካ ጉባኤ አስተዋፅኦ እንደማይከፍል ለወረዳ ቤተ ክህነት በጻፈው ደብዳቤ መፃፉን ደጀሰላም በዚሁ ዘገባው ጠቅሷል፡፡
ይኸው ዘገባ አያይዞ እንደገለፀው ከሆነም፣ የዛሬማ ወንዝ ላይ ሊሰራ የታቀደውን የግድብ ሥራ ተረክቦ ሲመራ የቆየው ሱር ኮንስትራክሽን ሥራውን አቋርጦ በመውጣት በምትኩ ለአንድ የቻይና ተቋራጭ ተሰጥቷል። ለዚህ ምክኒያት ይሆናሉ ተብለው ከተጠቀሱት ነገሮች ውስጥ፣ ቁፋሮው የሚካሄድበት ቦታ ከመሬት በሚፈልቅ ውኃ እየተሞላ ማስቸገሩ፣ እንዲሁም የምእመኑ ተቃውሞ ያሳደረው ግፊት ዋነኞቹ ናቸው። የዛሬማ ግድብ ስራ ንድፍ የተዘጋጀው በትግራይ ውኃ ሥራዎች ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሲሆን፣ የግንባታ ስራውን የሚያከናውነው ደግሞ የትግራይ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ነው።
መረጃውን በመንተራስ ኢሳት ወደ አካባቢው በመደወል እንዳረጋገጠው መነኮሳቱ እየተከዋከቡ ነው። የፌደራል ፖሊስ አባላት በአካባቢው በብዛት መስፈራቸውንም የአካባቢው ሰዎች ተናግረዋል። ዘገባውን ያጠናከረው የአውስትራሊያው ቅዱስ ሀብት በላቸው ነው።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide