ጥር ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-እጅግ በተለጠጠው የኢትዮጽያ መንግስት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት በያዝነው 2006 በጀት ግማሽ ዓመት የወጪ ንግዱ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ማሽቆልቆል ማሳየቱን ያገኘናቸው መረጃዎች ጠቆሙ፡፡
በ2006 ግማሽ የበጀት ዓመት ከሆርቲካልቸር እና ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኤክስፖርት የተገኘው ገቢ ከዕቅዱ አንጻር እጅግ አነስተኛ መሆኑ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ከሆርቲካልቸር ዘርፍ ማለትም አበባ ፣አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ለውጪ ገበያ በማቅረብ 202 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ማግኘት የተቻለው 106 ሚሊየን ዶላር ብቻ ነው፡፡
በቆዳና የቆዳ ውጤቶች ዘርፍም 142 ሚሊየን ዶላር በስድስት ወሩ ለማስገባት ታቅዶ ከግማሽ በታች ማለትም 68 ሚሊየን ዶላር ማሳካት መቻሉን ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
ለእቅዶቹ ማሽቆልቆል ዋንኛው ምክንያት መንግስት የያዘውን የተለጠጠ እቅድ ለማሳካት ሲባል ምንም ዓይነት ላኪዎችን የሚያተጋ ነገር ሳይፈጠር፣ የአሰራርና የአቅርቦት እንዲሁም አዳዲስ ገበያ ፍለጋ ስራ ሳይከናወን የተለጠጠ እቅድ በመያዙ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች አስረድተዋል፡፡ ይህም የገቢ ማነስ መንግስት ከአቅም በላይ በራሱ ገቢ ጭምር ለመስራት ቃል የገባቸው የቤቶች ልማት፣ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ማካሄጂያ በጀት እጥረት ሊያስከትልበት እንደሚችል ከወዲሁ ተገምቶአል፡፡
በሆርቲካልቸር ዘርፍ በርካታ ሰዎች ወደዘርፉ እንዲሰማሩ የሚያስችሉ ስራዎች በሚፈለገው መልክ መከናወን አለመቻሉ፣ለአዲስና ለማስፋፊያ ኢንቨስትመንቶች የመሬት አቅርቦት ችግሮች በተለይ በክልልች አካባቢ ማጋጠሙ ለእቅዶቹ ማሽቆልቆል በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ በከብት ሐብት ከአፍሪካ አንደኛ የመሆንዋ ጉዳይ የተለያዩ መረጃዎች ቢያሳዩም እርድ በበኣላት ወቅት ብቻ የሚከናወን መሆኑ የቆዳና ሌጦ እጥረት ዘርፉን እያሽመደመደው መሆኑ ታውቆአል፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙዎቹ ፋብሪካዎች ከማምረት አቅማቸው ከግማሽ በታች ለመንቀሳቀስ መገደዳቸው ተጠቁሞአል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍም ለመጀመሪያ ጊዜ ቆዳ ከጎረቤት አገር ከሱዳን እንዲሁም ከቻይና ጭምር ለማስመጣት መገደዱን መረጃው ያሳያል፡፡
በሆልቲካልቸር ዘርፍ የአምስት ኣመት ዕቅዱ ኤክስፖርትን ለማሳደግ አነስተኛ አርሶአደሮችንና አውትግሮዎርስን ባሳተፈ መልኩ በአትክልት በፍራፍሬና ኸርብስ ላይ ያተኮረ ልማት ይካሄዳል፡፡
የተሻሻሉ የሆልቲካልቸር የቅድመና ድህረ ምርት መመዘኛዎችንና ደረጃዎችን መሰረት ያደረገ የተጠናከረ የክትትልና የግምገማ ስርዓትን በማዳበር የአገራችን የሆልቲካልቸር ልማት የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ ትኩረት ይሰጣል ይላል፡፡ ዕቅዱ ሊጠናቀቅ አንድ ዓመት ብቻ ነው የቀረው።
የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅዱ በተጀመረበት 2003 ዓ.ም ከወጪ ንግድ ብቻ በጠቅላላው ከ3.2 ቢሊየን ዶላር በላይ እንደሚገኝ ታቅዶ የነበረ ሲሆን የተገኘው ግን 2.7 ቢሊየን ዶላር ነበር፡፡ በ2004 ዓ.ም 4.6 ቢሊየን ዶላር ታቅዶ ማሳካት የተቻለው 3.1 ቢሊየን ዶላር ነው፡፡
በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው የሚልኩት ገንዘብ ኢትዮጵያ ምርቶችን ወደ ውጭ ልካ ከምታገኘው ገንዘብ እየበለጠ መምጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።