የወጪ ንግድ መቀነስ በሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል ተባለ

ኢሳት (መጋቢት 1 ፥ 2008)

ባለፉት ስድስት ወራት የኢትዮጵያ ወጪ ንግድ ከተጠበቀው በታች ገቢ ማስገኘቱ በሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ተገለጠ።

ዝቅተኛ አፈጻጸም ተመዝግቦበታል በተባለው በዚሁ የስድስት ወራት የውጭ ንግድ 1.6 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጓን የመንግስት ባለስልጣናት ረቡዕ አስታውቀዋል።

በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለፓርላማ ሪፖርትን ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ የሃገሪቱ የውጭ ንግድ ገቢ ዝቅተኛ አፈጻጸም ማስመዝገቡንና ለገቢ ንግድ የሚውለው ገንዘብ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

የሃገሪቱ ወጭና ገቢ ንግድ ዝቅተኛ አፈጻጸም ማስመዝገቡንና ለገቢ ንግድ የሚውለው ገንዘብ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

የሃገሪቱ ወጪና ገቢ ንግድ ሊመጣጠን ባለመቻሉ ምክንያት የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እየተባባሰ መምጣቱንና ለኢኮኖሚው ፈታኝ ሆኖ መገኘቱን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አስታውቀዋል።

ይሁንና፣ በውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ላይ የተፈጠረውን ውጥረት ለመቀነስ መንግስት ከሃዋላ፣ በቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት እና ከውጭ ምንዛሪ ክምችት የተገኘውን ገንዘብ በመጠቀም ላይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላት አስረድተዋል።

ሃገሪቱ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ተከትሎ የብሄራዊ ባንክ በቅርቡ አዳዲስ የቁጥጥር ደንቦችን ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል።

በንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሃብቶ በበኩላቸው የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት በጣም መቸገራቸውንና የንግድ ስራቸውም ገቢው እያሽቆለቆለ መምጣቱን በመግለጽ ላይ ናቸው።

ሃገሪቱ አጋጥሟት ያለው ይኸው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን እንደሚያሳድርና የዋጋ ግሽበቱም እንደሚያባብሰው የአለም ባንክ ማሳሰቡ ይታወሳል።

አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በበኩላቸው በአጠቃላይ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ጉዞ ጤነኛ ነው በማለት ምላሽን የሰጡ ሲሆን፣ የአለም ባንክና ሌሎች አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ሃገሪቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባት በማሳሰብ ላይ ናቸው።