የወባ በሽታ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች አሳሳቢ ችግር ሆኖ መቀጠሉ ተገለጸ

ኢሳት (ታህሳስ 4 ፥ 2009)

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች የወባ በሽታ አሁንም ድረስ አሳሳቢ የጤና ችግር ሆኖ መቀጠሉንና ባለፈው አመት ብቻ ከ400 ሺ በላይ ሰዎች በዚሁ በሽታ መሞታቸውን የአለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

ከ400 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለወባ በሽታ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩባት ኢትዮጵያ ከበሽታው ነጻ ለመባል ስታካሄድ የቆየችው መጠነ ሰፊ ዘመቻ ሳይሳካ መቅረቱን ለመረዳት ተችሏል።

ኢትዮጵያ ከዚሁ የበሽታ ስርጭት ነጻ ለመባል ለተከታታይ ሶስት አመታት ጥረትን ስታደርግ ብትቆይም አሁንም ድረስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሃገሪቱ ዜጎች ለወባ በሽታ ተጋላጭ መሆናቸውን የአለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ያመለክታል።

ለተከታታይ ሶስት አመታት የወባ ስርጭት ያልታየባቸው ስሪላንካና ክርጊስታን  ከበሽታው ነጻ በመባል በአለም የጤና ድርጅት እውቅና የተሰጣቸው ብቸኛ ሃገራት ለመሆን ችለዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሃገራት የወባ በሽታ አሁንም ድረስ አሳሳቢ የጤና ችግር ሆኖ ቢቀጥልም፣ ባለፉት አምስት አመታት መድሃኒትን ለታካሚዎች የማቅረቡና የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የተደረጉ ጥረቶች ውጤት ማስመዝገባቸውን የአለም ጤና ድርጅት የ2015 ሪፖርቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

የጤና ድርጅቱ በቀጣዩ አራት አመታት 10 የአለማችን ሃገራት ከወባ በሽታ ስርጭት ነጻ እንዲሆኑ ለማድረግም አለም አቀፍ ዘመቻ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስታውቋል።

ባለፈው አመት በአለም ዙሪያ ከተመዘገቡ 429ሺ የወባ በሽታዎች ሞት መካከል 92 በመቶ የሚሆነው በአፍሪካ የደረስ ነው። በበሽታው ስርጭት ከተያዙ 2012 ሚሊዮን ሰዎች መካከልም 90 በመቶ የሚሆኑት በአህጉሪቱ የሚኖሩ መሆናቸውን የአለም አቀፍ ጤና ድርጅት ሪፖርት አመልክቷል።

የገንዘብ እጥረት፣ የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ እንዲሁም የጤና መሰረተ-ልማት በበቂ ሁኔታ አለመስፋፋት የበሽታው ስርጭት እልባት እንዲያገኝ አስተዋጽዖ ማድረጋቸው ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ካላት አጠቃላይ ህዝብ መካከል 60 በመቶ አካባቢ የሚሆነው ለወባ ትንኝ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ይኖራሉ። 75 በመቶ የሚሆነው የሃገሪቱ ክፍልም ለወባ በሽታ ስርጭት ተጋላጭ መሆኑን የአለም አቀፍ ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

የዚሁ በሽታ ስርጭት በተለይ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በየአመቱ የበርካታ ሰዎች ህይወትን እንደሚቀጥፍ ለመረዳት ተችሏል።