(ኢሳት ዲሲ–ጥር 15/2010)
በወልዲያ በቃና ዘገሊላ በአል ላይ በወጡ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ጅምላ ግድያ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አወገዘ።
ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ እንዳለው በመንግስት ታጣቂዎች የተፈጸመው ጅምላ ግድያ ገለልተኛ በሆነ አካል በአስቸኳይ ተጣርቶ ጥቃት ፈጻሚዎቹ ተጠያቂ መሆን ይኖርባቸዋል።
ጥቃቱን የሚፈጽሙ ያልሰለጠኑ የጸጥታ አካላትም ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጡ ትምህርት ሊሰጣቸው ይገባል ብሏል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የወልዲያው ጥቃት እጅግ ያሳሰበው መሆኑን ነው የገለጸው።
ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫም በወልድያ ለጥምቀት በአል በወጡ ሰዎች ላይ ጅምላ ግድያ በመንግስት አካላት መፈጸሙን ክፉኛ አውግዟል።
እንደ ኮሚሽኑ ገለጻ የመንግስት ታጣቂዎች ግድያውን የፈጸሙት አገዛዙን የሚቃወሙ ሰዎች መፈክር በማሰማታቸውና ስርአቱን ባለመደገፋቸው ነው።
ከጥቃቱ በኋላም ሕዝቡ መንገድ ከመዝጋት አንስቶ በንብረት ላይም ጉዳት አድርሷል ነው ያለው።
ይህ አላስፈላጊ ግድያ ገዥው ፓርቲ ለለውጥ ተዘጋጅቻለሁ ባለበት ማግስት መፈጸሙ በተገባው የተሃድሶ የቃል ርምጃ ላይ ጠባሳ እንደሚያሳርፍ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ገልጿል።
እናም የመንግስት ታጣቂዎች ስራቸውን በሚሰሩበት ጊዜ ከሃይል ርምጃ እንዲቆጠቡ የኮሚሽኑ መግለጫ አሳስቧል።
ምንም እንኳ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና ጉዳት ላይ ጥንቃቄ የተሞላበት ምርመራ ይካሄዳል ቢሉም ጉዳዩን ግን ገለልተኛ አካል ሊያጠራው እንደሚገባ ኮሚሽኑ አስገንዝቧል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንዳለው በወልዲያ ሰላማዊ ሰዎችን የገደሉ ታጣቂዎች ጉዳዩ ተጣርቶ ተጠያቂ መሆን ይኖርባቸዋል።
በሀገሪቱ በጸጥታ ማስከበር ስራ ላይ ለተሰማሩት አካላትም ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ሊሰጣቸው ይገባል ብሏል።
በወልድያው ጥቃት ከ13 በላይ ሰዎች መገደላቸው ሲነገር እስካሁን አገዛዙ ያመነው የሟቾች ቁጥር 7 ብቻ መሆኑን ነው።