የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እግር ኳስ ተጫዋቾችና የቡድን መሪ በመሃል ዳኛ እያሱ ፈንቴ ላይ ሜዳ ውስጥ ድብደባ መፈጸማቸውን ተከትሎ የሊጉ ጨዋታ ተቋረጠ

የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እግር ኳስ ተጫዋቾችና የቡድን መሪ በመሃል ዳኛ እያሱ ፈንቴ ላይ ሜዳ ውስጥ ድብደባ መፈጸማቸውን ተከትሎ የሊጉ ጨዋታ ተቋረጠ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 23 ቀን 2010 ዓ/ም) በትናትናው እለት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 22ኛው ሳምንት የጫወታ መርሃግብር ከቀኑ 11፡00 ሰዓት መከላከያ ከወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ በአዲስ አበባ ያደረጉት ጫወታ፣ የወልዋሎ ቡድን መሪና ተጫዋቾች በፈጸሙት ድርጊት ምክንያት ጨዋታው ተቋረጠ።
ጫወታው በተጀመረ በ22ኛው ደቂቃ ላይ በሪችሞንድ ኦዶንጎ ባስቆጠሩት ቀዳሚ ጎል አማካኝነት ወልዋሎዎች 1-0 የመሩ ሲሆን፣ በ32ኛው ደቂቃ ላይ መከላካያዎች በምንይሉ ወንድሙ አማካኝነት 1-1 አቻ ሆኑ። በዚሁ አቻ ውጤት የመጀመሪያ የጫወታ ጋማሽ ተጠናቀቀ። በሁለተኛው የጫወታ ክፍለጊዜ በ83ኛው ደቂቃ ላይ መከላከያዎች በፍጹም ገ/ማሪያም አማካኝነት ሁለተኛዋን ጎል አገቡ።
የገባብን ጎል መስመር ላለፈም በሚል ምክንያት የወልዋሎ ተጫዋቾችና የቡድን መሪ ወደ ሜዳ በመግባት ጫወታውን የመሩትን የፌደራል ዳኛ እያሱ ፈንቴን በመክበብ እያባረሩ መደብደብ ጀምሩ። ችግሮች ሲከሰቱ ተጫዋቾችንና ደጋፊዎችን የማረጋጋት ኃላፊነት የነበራቸው የቡድን መሪው አቶ ማሩ ገብረጻዲቅ ለጸቡ መነሻና መባባስ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ አድርገዋል።
የወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ እግር ኳስ ቡድን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በበኩሉ ድርጊቱ ከስፖርት መርህ ውጪ መሆኑን ኮንኖ ለተጫዋቾቹ ማስጠንቀቂያ በመስጠት የቡድን መሪውን ከሃላፊነት ማንሳቱን አስታውቋል። ኮሚቴው በተጫዋቾቹ ላይ የገንዘብ ቅጣት ሳይጥል በማስጠንቀቂያ ብቻ እንዲታለፉ መድረጉ ለቀጣይ እንዳይደገም የሚያደርግ መቀጣጫ አይሆንም ተብሎለታል።
የወልዋሎ ቡድን መሪና ተጫዋቾች በፈጸሙት ስፖርታዊ ጨዋነት የጎደለው ስርዓት አልበኝነት ምክንያት ከፌደራል ዳኛ እያሱ ፈንቴ በተጨማሪ የመከላከያዎቹ ምንይሉ ወንድሙና ፍጹም ገ/ማሪያም ላይም ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል። በአቅራቢያው ከነበሩት የጸጥታ አስከባሪዎች ይልቅ የመከላከያ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች ዳኛውን ለመታደግ የተሻለ ከለላ መስጠታቸው ደጋፊዎችን አሳዝኗል። ጫወታው በስርዓት አልበኝነት ምክንያት በ83ኛው ደቂቃ ላይ እንዲቋረጥ ተደርጓል።
ዛሬ ኳስ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ማኅበር በጁፒተር ሆቴል ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባው በቀጣይ ሳምንት የሚደረጉ የፕሪምየር ሊግ ጫወታዎች እንዲቋረጡ ውሳኔ ሳልፏል። በቀጣይም የፕሪምየር ሊጉ ጫወታዎች እንዴት መቀጠል እንዳለባቸው ለመወሰን እግር ኳስ ማኅበሩ ለሚያዝያ 25 ቀን 2010 ዓ.ም የሊጉ ቡድን ኃላፊዎች ጋር ለመወያየት ስብሰባ ጠርቷል። ይህን ዜና እስካጠናቀርንበት ሰዓት ድረስ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ማኅበር በወልዋሎ እግር ኳስ ቡድን መሪና ተጫዋቾች ላይ እስካሁን የጣለው እገዳ አልታወቀም።
በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር /ፊፋ/ ወርሃዊ የደረጃ ሰንጠረዥ የኢትዮጵያ ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድን ካለፈው ወር ስምንት ደረጃዎችን ወደ ኋላ በመንሸራተት ከዓለም 145ኛ ከአፍሪካ 41ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ይህን ደካማ የአገሪቱን እግር ኳስ ጠንክሮ ለመለወጥ ከመስራት ይልቅ በተደጋጋሚ ጊዜያት የስርዓት አልበኝነት በመላው አገሪቱ የእግር ኳስ ቡድኖች ደጋፊዎችና ተጫዋቾች እየተለመዱ መጥተዋል። ችግሩን ለአንዴና ለተመጨረሻ ጊዜ እልባት ለመስጠት የእግርኳስ ማኅበሩ በባለሙያዎች የታገዘ መዋቅር በመዘርጋት አጥፊዎች ላይ የማያዳግም ሊወሰድ ይገባዋል።