የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰጠውን መልስ ተቃወመ
(ኢሳት ዜና ሰኔ 19 ቀን 2010 ዓ/ም) ኮሚቴው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰኔ 4 ቀን 2010 ዓም የወልቃይት የአማራ ብሄርተኝነት አስመላሽ ኮሚቴ ያቀረበው የማንነት ይከበርልኝ ጥያቄ ህግን ተከትሎ ያልተካሄደ ነው በማለት ውድቅ ማድረጉን በጽኑ ተቃውሞአል።
የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በመግለጫው የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ኬርያ ኢብራሒም ጥያቄያቸውን ውደቅ ያደረጉባቸውን ምክንያቶች አቅርቧል። ምክንያቶቹም ጥያቄው ፣ በክልሉ በሚገኙት የተለያዩ የመስተዳድር እርከኖች ቀርቦ አጥጋቢ መፍትሔ ያልተሰጠው ስለመሆኑ ከቀረበው ማመልከቻ ማረጋገጥ ባለመቻሉ ፣ የነዋሪው ሕዝብ ወይም የብሔር፣ብሔረሰቡ መሆኑን ለማመልከት ከነዋሪው መሐከል ቢያንስ አምስት ከመቶ(5%) ወይም ከብሔር ፣ብሔረሰቡ አባላት ቢያንስ አምስት ከመቶ ስም ዝርዝር ፊርማ እና አድራሻ የያዘ ባለመሆኑ፣ እንደአስፈላጊነቱ ጥያቄ ባቀረበው የመስተዳድር አካል ባለስልጣን የተፃፈ ፌርማ እና ማሕተም ያረፈበት ባለመሆኑ፣ እንዲሁም ለምክር ቤቱ ጥያቄ ለማቅረብ የሚመጣ ግለሰብ ወይም ግለሰቦች ከጠያቂው ብሔር፣ብሔረሰብ፣ሕዝብ የተወከሉ ለመሆናቸው በቂ ማረጋገጫ ያላቀረቡ የሚሉት ይገኙበታል።
ኮሚቴው የፌዴሬሽን ምክርቤት አፈጉባኤ የተከበሩ ወይዘሮ ኬርያ ኢብራሒም በማንነታቸው የትግራይ ተወላጅ እና የሕ.ወ.ሓ.ት. ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በመሆናቸውና ሴትዮዋ ወልቃይት የትግራይ ማንነት አይገባዉም ብለው ጥያቄዉን በሀይል ለማፈን ከሚታትሩ ወገኖች አንዷ በመሆናቸው ከዘር ሐረግም ወገንታዊነታቸው ለትግራይ መስተዳድር ያሳዩበት መልስ መሆኑ ደብዳቤው ላይ በግልፅ ተመልክቷል ብሎአል።
የትግራይ መስተዳድር አካላትና የሕወሓት አመራሮች ለወልቃይት የማንነት ጥያቄ ይቅር እና ምላሽ መስጠት የጥያቄው እና የጠያቂው ማሕበረሰብ ስም ሲጠራ መስማት ምን ያህል እንደሚያማቸው ይታወቃል ያለው መግለጫው፣ ቢችሉ በጠያቂው ማሕበረ ሰብ ላይ የዘር ማፅዳት(Genoocide) እርምጃ ቢወስዱ ለደስታቸው ወሰን ወደር አይገኝለትም ብሎአል፡፡
23 ሺ የፈራሚዎች ስም ዝርዝር እና ፊርማ በተወካዮቹ አማካኝነት ለፌዴሬሽን ምክርቤት መቅረቡን ያስታወሰው ኮሚቴው ፣ የሕጉ ድንጋጌ ከፊርማ አንፃር ከአጠቃላይ ነዋሪው ቢያንስ 5ሺ ቢፈርም እንደሚያስኬድ ያስቀመጠ ቢሆንም፣ የወይዘሮዋ ከሕግ በላይ የሆነ የራስ ድንጋጌ ከሕጉ ጋር ፍፁም ተቃራኒ ሁኖ እናገኘዋለን ብሎአል።
የትግራይ መስተዳድር አካላት ይቅር እና በፊርማቸው እና በማሕተማቸው ጥያቄዉን ዕውቅና ሊሰጡት፣ ማንነት ለጠየቀው የሕብረተሰብ ክፍል በላምባዲና እየተፈለገ እንዲታሰር እና የመኖሪያ ቀዬውን ጥሎ እንዲሰደድ እያደረጉ በመሆኑ ከእነሱ የእውቅና ደብዳቤ ማምጣት አይቻልም ሲል ኮሚቴው አስታውቋል።
የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላት በመጨረሻም ወይዘሮ ኬርያ ኢብራሒም የአፈናው ተቀጥላ በመሆን የትግራይ ክልል መስተዳድር አካላት ተልዕኮ በማንገብ እና የመንግስት ስልጣን በመጠቀም በተንሸዋረረ ዕይታ ኢ-ሕገመንግስታዊ የሆነ የግል ፍላጎታቸው እና ዐላማቸው የሚያሳካ ደብዳቤ መጻፋቸውን ጠቅሰው ፣ የሳቸው ደብዳቤ በሐገሪቱ የመጨረሻ ደብዳቤ እና ውሳኔ ሊሆን ስለማይችል ኮሚቴው ጉዳዩን በመያዝ በየደረጃው ከጠቅላይሚኒስትሩ እስከ ፍርድቤት ድረስ የሚሔድ መሆኑን አስታውቋል።