የካቲት ፴ (ሠላሳ)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከክልሉ ጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፣ “ስለወልቃይት ጉዳይ የሚያገባው የትግራይ ክልልና የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንጅ የአማራ ክልል አይደለም” ብለዋል።
“ በወልቃይት፣ በራያ እና ሌሎችም አካባቢዎች፣የትግራይ ክልል ከአማራ ክልል መሬት እየወሰደ ነው፣ ዳሸን ተራራና ላሊበላ ሳይቀር የእኔ ነው እያለ ነው፤ በየጊዜውም በትግራይ መገናኛ ብዙሃን የታጠቁ ሰዎች እየቀረቡ ሽለላ ያሰማሉ፣ በአማራ ክልል በተቃራኒው አገራዊ ሙዚቃ እንኳን እንዳናሰማ እንከለካለን” የሚሉና ሌሎችንም በርካታ ጥያቄዎችን በጽሁፍ ያቀረቡት ጋዜጠኞች፣ ከአቶ ንጉሱ ጥላሁን አጥጋቢ መልስ አለማግኘታቸውን ይናገራሉ። አቶ ንገሱ “የወልቃይት ህዝብ ተቃውሞ ባሰማ የባህርዳር ፣ የጎንደር ፣ የዳንግላ፣ የመራዊ ህዝብ ምን አገባው? ድንበር ላይ በተነሳ ጥያቄ፣ ማሃሉ ለምን ይቃጠላል?” የሚል ህዝብን የሚከፋፍልና የአንዱ አካባቢ ህዝብ ለሌላው እንደማይመለከተው የሚያሳይ መልስ ሰጥተዋል። “ የቅማንት ጥያቄ በአማራ ክልል በቅድሚያ እንደሚታየው፣ የቁጫ ጥያቄ በደቡብ ክልል እንደሚታየው ሁሉ፣ የወልቃይት ጥያቄም በትግራይ ክልል መንግስት መታየት ሲገባው፣ ጎንደርን የሚያቃጥልበት፣ ባህርዳርን የሚያቃጥልበት፣ ደብረታቦርን የሚያቃጥልበት፣ አማራ ክልልን የሚያቃጥልበት አንዳች ምክንያት የለም” በማለት የብአዴንን አቋም ግልጽ አድርገዋል።