የወልቃይት የማንነት ጥያቄ የኮሚቴ አባል አቶ ሊላይ ብርሃኔ ፍርድ ቤት ቀረበ

ኢሳት (መጋቢት 27 ፥ 2008)

የወልቃይት ተወላጆችን የማንነት ጥያቄ አንስተው እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙ የኮሚቴ አባላት አንዱ የሆነውና ለሳምንታት የተሰወረው አቶ ሊላይ ብርሃኔ ሰኞ ዕለት ፍ/ቤት ቀረበ።

ሁመራ ፍርድ ቤት የቀረበው ሊላይ ብርሃኔ ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመበት ገልጿል።

የተደበደብኩት አማራነቴን ስለጠየኩ ነው በማለት ለፍ/ቤት ተቃውሞ ማሰማቱን የአይን ምስክሮች ለኢሳት ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ ያለው አባተ ስምና ፊርማ የወጣው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው የወልቃይት ህዝብ ማንነትን የጠየቁ ወገኖች ጥር 28 እና የካቲት 19, 2008 ዕም አቤቱታ አቅርበዋል። በአቤቱታቸውም የወልቃይት ህዝብ ማንነትና ተያያዥ ህገመንግስታዊ ጥያቄዎች እንደተነሱ ያብራራል።

የፌዴሬሽን ም/ቤት ጉዳዩ በቅድሚያ ከትግራይ ክልላዊ መንግስት ይቅረብ በማለት ወደዚያ መርቶታል።

ሆኖም አቤቱታ አቅራቢዎች ለትግራይ ክልል መንግስት ያቀረቡት አቤቱታ ተቀባይነት አለማግኘቱ፣ ይልቁንም ወንደለኞች ናችሁ እየተባሉ በመሳደድ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።