የወልቃይት ማንነት ጥያቄ በሃገሪቱ ለተከሰቱት ህዝባዊ ተቃውሞዎች መነሻ በመሆኑ ባስቸኳይ ይፈታ ዘንድ  የምክር ቤት አባላት ጠየቁ

ኅዳር ፲፫ (አሥራ ሦስት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የአማራ ክልል ምክር ቤት በሚያካሂደው ጉባዔ ላይ የተገኙ የልዩ ልዩ ወረዳ ተወካዮች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ላይ ባነሱት ጥያቄ የድንበር መካለሉ ጉዳይ ለበርካታ የሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኖ እያለ ምክር ቤቱ ባቀረበው ሪፖርት ጉዳዩ ወደ የሚመለከተው አካል ተላልፏል መባሉ እንዳልተዋጠላቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

በክልሉ ለተከሰተው ህዝባዊ ተቃውሞ መንስዔ የመንግስት የመዘናጋት ውጤት እንደሆነ የተናገሩት የአዳርቃይ ወረዳ ደባርቅ ምርጫ ክልል ምክር ቤት ተወካይ አቶ ተፈሪ አቡኃይ፣  በተከሰተው ግጭት የወደመው ንብረትና ህይወት ጥፋት የተከሰተው በወቅቱ ሊወሰዱ የሚገባቸው ጥያቄዎች ወቅታቸውን በጠበቀ ሁኔታ ከመፍታት ይልቅ ለማዳፈን መሞከሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከደምቢያ ቁጠር አንድ የምርጫ ጣቢያ የህዝብ ተወካይ የሆኑት  ቄስ አዲስ ሳህሌ እንደተናገሩት ከክልሉ ከፍተኛ ውድመት የደረሰው በአካባቢው እንደሆነ ተናግረው፤ ከህዝባዊ አመጹ በፊት የአካባቢው ነዋሪ የሚያቀርቡትን የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎች  ተቀብሎ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ያጠፉ አመራርሮችን መልሰው  በቦታቸው በመተው  ህብረተሰቡን ሲያንገላቱ መቆየታቸው አንዱ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በፌደራል ደረጃ የሚገኙ የብአዴን አመራር አካላት በክልሉ ለተከሰቱት የድንበር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጥ በተለያዩ የጎንደር ዩኒቨርስቲ ምሁራንና የከተማዋ አንጋፋ ነዋሪዎች ቢጠየቅም አመራሮች ግን  ዝምታን መምረጣቸው አሳፋሪ መሆኑን በድፍረት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ አሁንም በሪፖርቱ ተስፋ አለን የሚለው አነጋገር የሚያዋጣ ስላልሆነ ፍጥነትን በመጨመር የድንበሩ ጉዳይ አሁንም ምላሽ ያስፈልገዋል፡፡ የቡግና ወረዳ ሰሜን ወሎ የህዝብ ተወካይ በሰጡት አስተያየት የድንበሩ ጉዳይ ‹‹ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ይፈታል በሚል የቀረበው ሪፖርት ለምክር ቤቱ አባላት ግልጽ ሆኖ ሊቀመጥ ይገባል ›› በማለት ‹‹ ውጤቱስ መቸ ሊገለጽ ነው? ›› የሚል ጥያቄ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡ይህ ጥያቄ በአስቸኳይ ካልተመለሰ ከአሁን በፊት የተከሰተው ህዝባዊ ተቃውሞ ተመልሶ ሊቀሰቀስ እንደሚችል ላቸውን ስጋት ተናግረዋል፡፡

በክልሎች መካከል በሚነሱ የድንበር አለመግባባቶች ጉዳዩን የፌደራል መንግስትችግሩን እንደሚፈታ በህገ መንግስቱ ቢደነገግም የፌደራል መንግስቱ ግን በዝምታ በማየት እሰካሁን ለምን ቆየ? በማለት ጥያቄ ያቀረቡት የመቄት ምርጫ ክልል ተወካይ ቄስ ካሳ ጌታሁን ናቸው፡፡ ግጭት በተፈጠረባቸውም ሆነ ባልተፈጠረባቸው በሁሉም አካባቢዎች ከህጻናት ጀምሮ እስከ አዋቂው ድረስ የመነጋገሪያ ርዕስ እስኪሆን የፌደራል አመራሮች እንዳልሰሙ በመሆን የድንበሩን ጉዳይ ችላ ማለታቸው አግባብ አለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

ኢህአዴግ ከአመጣጡ ጀምሮ በብዙ መስዋዕትነት ስልጣን እደያዘ ይታወቃል፡፡የአመራሩ ባህሪ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ በሃሪው ገጽታውን እየተቀየረ መምጣቱ ህብረተሰቡን እያስቆጣ መጥቷል፡፡በበርካታ ልማቶች ላይ የጥራት ጉድለት ሲታይ በዝምታ የማየት ሁኔታ በማዘውተሩ፣ ህብረተሰቡ በድርጅቱ ላይ ያለውን አመኔታ ተሸርሽሮ እንዲያልቅ ማድረጉን ተወካዩ ተናግረዋል፡፡

በአዊ ዞን የዳንግላ ወረዳ የህዘብ ተወካይ ወይዘሮ ቀናሰው በቀለ እንደተናገሩት መቅደም ያለበት ሁኔታና የህዝብ ጥያቄ ቀድሞ መመለስ እንዳለበት ተናግረው፣ የአካባቢያችን ህዝብ በድንበሩ ዙሪያ ምን ተወሰነ የሚለውን ጥያቄ በቀዳሚነት የሚጠየቅ በመሆኑ የድንበሩ ጉዳይ ለሚመለከተው አካል ተሰጥቷል የሚለው ምላሽ አጥጋቢ ስላልሆነ በአስቸኳይ ምላሽ ይሰጠው ዘንድ ምክር ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት አመራሮች በተለይ በድንበር ዙሪያ ያለውን ሁኔታ አድበስብሰው በማለፍ በቁርጠኝነት ለመመለስ ሲቸገሩ ታይተዋል።