ኢሳት (ታህሳስ 19 ፥ 2009)
በኮ/ል ደመቀ ዘውዱና በሌሎች የወልቃይት ማንነት ኮሚቴ አባላት ላይ በአዲስ አበባ የተመሰረተው ክስ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ማክሰኞች እለት የታየ ቢሆንም፣ ኮ/ል ደመቀ አሁንም በጎንደር ወህኒ ቤት ይገኛሉ። አቶ አታላይ ዛፌ፣ አቶ መብራቱ ጌታሁን፣ አቶ አለነ ሻማ፣ አቶ ጌታቸው አደመ፣ እንዲሁም ነጋ ባንቲሁን፣ ማክሰኞ ታህሳስ 18, 2009 ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፣ ተለዋጭ ቀጠሮ ለጥር 4 ፥ 2009 ተሰጥቷቸው ወደ ወህኒ ቤት ተመልሰዋል።
በሌላ በኩል የህወሃት ደጋፊ ድረገጾች የአማራ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከስልጣን እንዲወርዱ ጥሪ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።
ገዱ አንዳርጋቸውም ሆነ ደመቀ መኮንን ለዚህ ስፍራና ስልጣን የበቃችሁት በትግራይ ልጆች መስዋዕትነት ነው በማለት ያለህወሃት ምንም ናቸሁ በማለት አሳስበዋቸዋል።
ታህሳስ 5 ቀን 2009 በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት “በወልቃይት ህዝብ የአማራ ብሄርተኝነት ማንነት ጥያቄ ኮሚቴ አባላት ላይ የተመሰረተው ክስ ህገመንግስታዊውን ስርዓት በሃይል የማፍረስ አላማ ይዞ አላማውን ለማስፈጸም እና በመንግስት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር እንዲሁም ህብረተሰቡን ለማስፈራራት የሃገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ህገመንግስታዊ፣ ኢኮኖሚያው ወይም ማህበራዊ ተቋማትን ለማናጋት እና ለማፈራረስ ተብሎ የሚንቀሳቀሰውን አርበኞች ግንቦት 7 ተብሎ የሚጠራውን የሽብር ቡድን ተልዕኮ ለማስፈጸም፣ የወልቃይት ህዝብ የአማራ ብሄርተኝነት ማንነት ጥያቄ ኮሚቴ በማቋቋም በዚያ ሽፋን ከሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት በመመስረት በትግራይ ክልልዊ መንግስትና በወልቃይት መስተዳደሮች ላይ የግድያ እና አፈና እርምጃ እንደተወሰድባቸው ለወጣቶች የጦር መሳሪያ አስታጥቀው መንቀሳቀሳቸውን ይዘረዝራል።
ኮ/ል ደመቀን ለመያዝ የጸጥታ ሃይሎች በተንቀሳቀሱበት ወቅት ሃምሌ 5 ፥ 2008 ተከሰተ ያለውን ሁኔታ አቃቤ ህግ በክሱ ዘርዝሯል። በዚህም ኮማንደር ሃለፎም አዳነን ጨምሮ 10 ፖሊሶችን በጥይትና በቦምብ በመግደል እንዲሁም ሌሎች 7 ፖሊሶችን በማቁሰል የሽብር ተግባር ፈጽመዋል በማለት ይከሳል።
ከሃምሌ 5፣ 2007 ጀምሮ እስከ ነሃሴ 25 ፥ 2008, በሰሜን ጎንደር ዙሪያ ደባርቅ፣ ወሮታ፣ ደምቢያ፣ ወገራ፣ በምራብ አርማጭሆ፣ በመተማ ዮሃንስ፣ በመተማ ዙሪያ ባስነሱት አመጽ ከ95 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት እንዲወድም አድርገዋል በማለት ከስሷል።
በዚህም የህወሃት ንብረት የሆነው የሰሌዳ ቁጥሩ 6/630 ሰላም አውቶቡስ መቃጠሉም በክሱ ውስጥ ተጠቅሷል። በጎንደር ከተማ በሚገኙ ቀበሌዎች በመንግስትና በህዝብ ተቋማት በተሽከርካሪዎች ላይ የ10 ሚሊዮን 679ሺ 945 ብር ውድመት መከተሉም በክሱ ተዘርዝሯል።
ከጎንደር ባሻገር ከነሃሴ 18 እስከ 24 2009 በምዕራብ ጎጃም በሚገኙ በባህርዳር ዙሪያ፣ በመርዓዊ ከተማ፣ በሜጫ ወረዳ፣ በቡሬ፣ ደጋ ዳሞት፣ አዴት ከተማ በፍኖተሰላም እና በባህርዳር ከተማ ከ95 ሚሊዮን 345ሺ ብር በላይ የሚገመት ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ አድርጋችኋል በሚል ተከሰዋል።
ይህ ክስ በቅድሚያ በኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ላይ በአማራ ክልል የቀረበ ሲሆን፣ አሁን ሌሎች የኮሚቴ አባላትን ጨምሮ ከታህሳስ 5፣ 2009 ጀምሮ በአዲስ አበባ ፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በመታየት ላይ ይገኛል። ማክሰኞ ታህሳስ 18, 2009 ለሁለተኛ ጊዜ የቀረቡት አቶ አታላይ ዛፌ፣ አቶ መብራቱ ጥላሁን አቶ አለነ ሻማ፣ አቶ ጌታቸው አደራ፣ አቶ ነጋ ባንቲሁን፣ ለፊታችን ጥር 4 ፥ 2009 ለሶስተኛ ጊዜ ተቀጥረዋል።
አቃቤ ህግ ምርመራዬን ስላልጨረስኩ ሌሎች የሚመረመሩ ሰዎች ስላሉ በሚል ባቀረበው ጥያቄ ፍ/ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ከወልቃይት የአማራ ማንነት የኮሚቴ አባላት 6ቱ በማዕከላዊ ምርመራ እስር ቤት ሲገኙ፣ 9ኙ በዳንሻ ወህኒ ቤት መሆናቸው ተመልክቷል። ከኮሚቴ አባላቱ ሶስቱ የተሰደዱ ሲሆን፣ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ አሁንም በጎንደር ወህኒ ቤት ይገኛሉ። እርሳቸውን ከጎንደር ወህኔ ቤት ወደ አዲስ አበባ ለመውሰድ በመንግስት በኩል በርካታ ጥረቶች ቢካሄዱም፣ በህዝባዊ ግፊትና ተቃውሞ መገታቱ ይታወቃል።