(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 14/2011) የወላይታ ዲቻ እግር ኳስ ክለብ ከደቡብ ፖሊስ ጋር የሚደረገው ጨዋታ በገለልተኛ ሜዳ እንዲካሄድ ጠየቀ።
የእግር ኳስ ክለቡ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጻፈው ደብዳቤ ቅዳሜ ዕለት በሃዋሳ ከተማ ሊደረግ የነበረው ጨዋታ በደጋፊዎቹና በንብረቱ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ጠቅሶ ከሀዋሳ ውጪ በገለልተኛ ቦታ እንዲደረግ ጥያቄ አቅርቧል።
የሃዋሳ ከተማ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ሳይካሄድ መቅረቱን አስታውቋል።
በዕለቱ ግጭት 18 ሰዎች መጎዳታቸውን፣ የመንግስትና የግለሰቦች ንብረት የሆኑ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት መድረሱንም የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ገልጿል።
ከግጭቱ ጋር በተያያዘም 37 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተመልክቷል።
ቅዳሜ ዕለት በሀዋሳ ከተማ ሊደረግ የነበረው የወላይታ ዲቻና የደቡብ ፖሊስ የእግር ኳስ ቡድኖች ጨዋታ የተሰረዘው በጸጥታ ችግር ነው ሲል የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ዛሬ አስታውቋል።
የአስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ደስታ ዶጊሶ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች መል በተፈጠረ አለመግባባት ጨዋታው ሳይካሄድ ቀርቷል።
የወላይታ ዲቻ እግር ኳስ ክለብ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጻፈው ደብዳቤ ግን ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከሰጠው መግለጫ ጋር የሚቃረን ነው።
ክለቡ ቀደም ብሎ ይህ ችግር እንደሚፈጠር በመጠቆም የጨዋታው ሜዳ እንዲቀየር መጠየቁን ከገለጸ በኋላ ስጋታችንን የሚያረጋግጥ ተግባር ነው የተፈጸመው ሲል በደብዳቤው አመልክቷል።
የወላይታ ዲቻ ክለብ ተጫዋቾችና አመራሮች ለውድድሩ ሀዋሳ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ በሆቴላቸውና በልምምድ ቦታ በመምጣት በስድብና ዛቻ ስጋት ውስጥ እንዲገቡ መደረጋቸውን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተጻፈው ደብዳቤ ላይ ተገልጿል።
በውድድሩ ዕለትም ወደ ሜዳ ከገቡ በኋላ በደጋፊዎቻቸውና በተሽከርካሪዎች ላይ ከባድ ጉዳት የሚያደርስ ጥቃት መፈጸሙን የወላይታ ዲቻ እግር ኳስ ክለብ አስታውቋል።
በዚህ መልኩ ጨዋታውን ለማካሄድ ስለማይቻል በገለልተኛ ሜዳ እንዲደረግ ክለቡ ጠይቋል።
የሀዋሳ ከተማ የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ታደሰ ዶጊሶ ሁለቱንም ወገኖች ለችግሩ ተጠያቂ በሚያደርግ መልኩ የሰጡትን መግለጫ የወላይታ ዲቻ እግር ኳስ ክለብ እንደማይቀበለው ኢሳት ያነጋገራቸው የክለቡ አመራሮች ገልጸዋል።
ግልጽ የሆነ፣ በተደራጀ መልኩ የተካሄደ ጥቃት ተፈጽሞብናል ብለዋል አመራሮቹ።
አቶ ታደሰ በዕለቱ በነበረው የጸጥታ ችግር በአንዲት ሴት ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱንና በሌሎች 17 ሰዎች ላይም ጥቃቱ መፈጸሙን ተናግረዋል።
የመንግስትና የግል ተሽከርካሪዎች ላይም ጉዳት መድረሱን የገለጹት አቶ ታደሰ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 37 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።
የወላይታ ዲቻ እግር ኳስ ክለብ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያቀረበው ደብዳቤ በገለልተኛ ሜዳ እንዲሆን የሚጠይቅ ቢሆንም በየትኛው ሜዳ እንደሆነ አልተገለጸም።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በጉዳዩ ላይ እስከአሁን የሰጠው መልስ የለም።
በሌላ በኩል ከሀዋሳ ከተማ የእግር ኳስ ቡድን ጋር ለመጫወት ሀዋሳ የገባው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን በጸጥታው ችግር ምክንያት ወደአዲስ አበባ መመለሱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ትላንት ሊደረግ የነበረው ጨዋታ የተሰረዘው ቅዳሜ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት መሆኑም ተመልክቷል።
የሀዋሳ ከተማ ጸጥታ የሚያስከብረው አካል የውድድሩን ጸጥታና ሰላም ለማስከበር ሃላፊነት መውሰድ አለመፈለጉን የሚጠቅሱት ምንጮች ጨዋታው ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም መወሰኑን ገልጸዋል።