(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 9/2011)በወላይታ ሶዶ የተካሄደውና የወላይታ ሕዝብን ጥያቄ ያስተናገደው ሕዝባዊ ሰልፍ በሰላም መጠናቀቁ ተገለጸ።
ሰልፈኞቹ የክልል እንሁን ጥያቄን ጨምሮ ባለ አምስት ነጥቦችን የያዘ ጥያቄን ለሚመለከተው አካል ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
ሰልፈኞቹ ለኢሳት እንዳሉት ማንነትን መሰረት አድርጎ በወላይታ ህዝብ ላይ የሚደርሰው ጥቃት ይቁም፣ወንጀለኞች ለህግ ይቅረቡ የሚሉና ሃገራዊ ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የህግ የበላይነት ይከበር የሚሉ መልዕክቶች ተላልፈዋል።
የወላይታ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር ዶክተር ብስራት ኤልያስ ለኢሳት እንዳሉት የወላይታ ህዝብ መብቴ ይከበር የሚል ጥያቄ ሲያቀርብ ዛሬ የመጀመሪያው አይደለም።
በዞኑ ለውጥ እንዲመጣ ብዙ ትግሎች ተካሂደዋል የዛሬው ሕዝባዊ ሰልፍም ይህንን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
ማለዳ 12 ላይ ተጀመረ የተባለውና በርካታ መልዕክቶችን አስተላልፎ የተጠናቀቀው የወላይታ ተወላጆች ሰልፍ ባለ አምስት ነጥብ ጥያቄዎችን አንግቦ እንደነበር ከስፍራው ለኢሳት የደረሱት መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከአጎራባች ህዝቦች ጋር ያለን አብሮነታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል፣የክልል ጥያቄያችን በአስቸኳይ ይመለስ፣የወላይታ ህዝብ በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ አንድነትን ይደግፋል የሚሉና ሌሎች ደግሞ በሰልፉ ላይ የተላለፉ መልዕክቶች ናቸው።
የተለያዩ ማህበራት እንዳስተባበሩት የተገለጸው ይሄ ሰልፍ የወላይታ ህዝብ በየጊዜው ለሚደርስበትና እየደረሰብት ላለው በደል መፍትሄም የሚጠይቅ ነው ብለዋል ሰልፈኞቹ ለኢሳት።
የወላይታ ህዝብ በየትኛውም አካባቢው ተዘዋውሮ የመስራት ኢትዮጵያዊ መብቱ ሊከበርለት ይገባል ሲሉ ሰልፈኞቹ መጠየቃቸውም ተገልጿል።
የወላይታ ህዝብ ለረጅም ጊዜ ራሱን በራሱ የማስተዳደርን መብት ከመጠየቅ ጀምሮ የወላይታ ህዝብ የሚፈልጋቸውን መሰረታዊ ጥያቄዎች ሲያቀርብ ነው የቆየው ያሉት ደግሞ ዶክተር ብስራት ኤልያስ ናቸው የወላይታ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር ከኢሳት ጋር በነበራቸው ቆይታ።
የወላይታ ህዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ዛሬ ላይ የተጀመሩ አይደሉም ዶክተር ብስራት ምላሽ ባለማግኘታቸው ግን እስካሁን የወላይታ ህዝብ እየተሰቃየ ነው ብለዋል።
እንደ ሃገር የመጣው ለውጥ የወላይታ ህዝብ ጋ አልደረሰም ብለዋል ዶክተር ብስራት።
ይሄ በመሆኑም የወላይታ ህዝብ በተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ከማንሳት ወደኋላ አላለም ብለዋል።
አሁንም ቢሆን መመለስ ያለባቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች አሉ ብለዋል ዶክተር ብስራት ኤልያስ