የኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎችን ቤት ለማዳረስ ከ20 ዓመታት በላይ እንደሚፈጅ አንድ ሰነድ አመለከተ

ነሃሴ ፲፮(አስራ ስድስት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በከንቲባ ድሪባ ኩማ የሚመራው አዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ረቂቅ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ የኮንዶሚየም ቤት ፈላጊዎችን ለማስተናገድ ከ20 ዓመታት በላይ ጊዜ እንደሚወስድ ጠቆሟል።

አስተዳደሩ ለኮንዶሚየም ቤቶች ብቻ ከ800ሺ በላይ ዜጎችን ቢመዘግብም በቀጣይ አምስት ዓመት ለመስራት ያቀደው 178 ሺ ቤቶችን ብቻ ነው፡፡

አስተዳደሩ ከ2006 እስከ 2010 ዓ.ም ሥራ ላይ አውለዋለሁ ባለው የስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ የቤቶች ልማትን በተመለከተ የያዘው ዕቅድ እጅግ አነስተኛ ሆኖ መገኘት በየደረጃው ያሉ አባላትና ካድሬዎችን ጭምር አስደንግጦአል፡፡

በአሁኑ ወቅት 20 በ80 በሚባለው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ባለቤት ለመሆን ከ800ሺ በላይ
ነዋሪዎች ተመዝግበው እየተጠባበቁ ባሉበት ሁኔታ በአምስት ዓመት 178ሺ ቤቶችን ብቻ እገነባለሁ በሚለው ስሌት ሲታሰብ 800ሺ ተመዝጋቢውን ለማዳረስ ከ20 ዓመታት በላይ ጊዜ የሚፈጅ መሆኑ ሕዝቡን በከፍተኛ ደረጃ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው ተብሎ ተሰግቶአል፡፡

የቤቶች ልማት ቢሮው ይህን ዕቅድ የያዘው የአስተዳደሩን አቅምና የእስካሁኑን የግንባታ ልምድ ግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን መረጃው ያመለክታል፡፡ የኩማ አስተዳደር በአምስት ዓመት ቆይታው 36ሺ700 ከባለአደራ አስተዳደር የተረከበውን ቤቶች ጨምሮ በጠቅላላው በሰልጣን ጊዜው መገንባት የቻለው 175ሺ246 ያህል ቤቶችን ብቻ ነው፡፡

ፕሮግራሙ ከተጀመረ ባለፉት ስምንት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለተጠቃሚዎች የተላለፉ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ብዛት 100 ሺ 559 ያህል ነው፡፡ አዲሱ ዕቅድም ሲሰራም ይህን የመገንባት አቅም ታሳቢ አድርጎ መሆኑን ታውቋል፡፡

ይህ ረቂቅ ዕቅድ የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በተገኙበት ሰሞኑን በየደረጃው ላሉ
የአስተዳደር አካላት ለውይይት በቀረበበት ወቅት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ አንዳንድ ተሰብሳቢዎች በዚሁ መድረክ ላይ ይህን ዕቅድ ሕዝቡ አይቀበለንም፣ ማሳመንም አንችልም በሚል ተሻሽሎ እንዲቀርብ ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም በአዲሱና አወዛጋቢ በነበረው የሊዝ አዋጅ መሠረት በቀጣይ አምስት ዓመታት በአዲስአበባ ብቻ ካሉ ነባር ባለይዞታዎች ግማሽ ያህሉን ወደሊዝ ሥርዓት ለማስገባት የተያዘው ዕቅድም በተመሳሳይ ሁኔታ በራሱ አመራር አባላት ተቃውሞ ገጥሞታል።

የሊዝ አዋጁ ነባር ይዞታን በተመለከተ ይዞታዎች ሲሸጡ ወደአዲሱ የሊዝ ሥርዓት እየገቡ እንደሚሄዱ ቢደነግግም  አስተዳደሩ በምን መልኩ 50 በመቶ ያህል ነባር ይዞታዎችን ወደሊዝ ሥርዓት
ለማስገባት እንዳቀደ ግልጽ አይደለም ፡፡

የስብሰባው ተካፋዮችም ይህ የሊዝ ጉዳይ አገር አቀፍ ሕግ ሆኖ ሳለ በአዲስአበባ ይጀመር የመባሉ ጉዳይ እና የአፈጻጸሙ ሁኔታ የህዝብን ድጋፍ ያሳጣል በሚል ሳይቀበሉት ቀርተዋል፡፡ ይህ የአምስት ዓመት የስትራቴጂክ ዕቅድ በቀጣይ ህብረተሰቡ ተወያይቶበት ስራ ላይ ይውላል ተብሎአል፡፡