ኢሳት (ሰኔ 21 ፥ 2008)
የኮንሶ ወረዳ ነዋሪዎች ወረዳዋ የተሻለ እድገት እንዲኖራት በማለት ወደ ዞን እንድትሻገር ሲሉ ያቀረቡትን ጥያቄ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ውድቅ ማድረጉ ተገለጸ።
በኮንሶ የተነሳው ራስን የማስተዳደር ጥያቄ በተወሰኑ ጥቂት ሰዎች የተጠየቀ እንጂ የአብዛኛው ህዝብ ጥያቄ አይደለም ያለው የደቡብ ክልል መንግስት ምክር ቤት፣ ጥያቄው ተቀባይነት የለውም ሲል በመንግስት መገናኛ ብዙሃን አስታውቋል።
የኮንሶ የራስ አስተዳደር ጥያቄ አስተባባሪዎች በበኩላቸው ውሳኔውን በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ከመስማት ውጪ ለኮንሶ ህዝብ የተላለፈው ምንም መልዕክት አለመኖሩን ተናግረዋል።
ውሳኔውን ተከትሎ በኮንሶ ክፍተኛ አደጋ እያንዣበበ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። ህዝቡ በምሬት ላይ በመሆኑ አዲስ የትግል አቅጣጫ ለመቀየስ እንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ ነዋሪዎች ለኢሳት በሰጡት ቃለምልልስ ተናግረዋል። ህጋዊ መንገድን በትዕግስት መጠቀም አለብን ያሉት አንድ ነዋሪ፣ ጥያቄያቸው አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘው እስከህይወት መስዋዕትነት ድረስ ትግል እንደሚያደርጉ ለኢሳት በሰጡት ቃለምልልስ ገልጸዋል።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት የኮንሶ ነዋሪዎች በበኩላቸው መላውን የኮንሶ ህዝብ አስተዳደራዊ ጥያቄ አቅርቦ እያለ፣ “ጥቂት ግለሰቦች” እየተባሉት በመንግስት መገናኛ ብዙሃን መጠቀሳቸው እንዳስግረማቸው ገልጸዋል። አስተዳደራዊ ጥያቄው የሁሉም ጥያቄ በመሆኑ መንግስት ለጥያቄው ቀና ምላሽ እንዲሰጥ ነዋሪዎቹ በአጽንዖት ጠይቀዋል።
ኢሳት ያነጋገራቸው የኮንሶ ነዋሪዎች አሁን የተሰጠውን የመንግስት ውሳኔ በምንም መልኩ እንደማይቀበሉ ተናግረዋል።
በወረዳዋ ሰፍረው የሚገኙ የጸጥታ ሃይሎች ከአስተዳደራዊ ጥያቄ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሰዎችን እያሰሩ እንደሆነ ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስታውቀዋል። በቅርቡም ለእስር ከተዳረጉ ነዋሪዎች በተጨማሪ አራት ሰዎች የገቡበት አለመታወቁንና ግድያ የተፈጸመባቸውአቶ ጃሚነ አያኖ የተባሉ የኮንሶ ነዋሪ በፌዴራል የጸጥታ ሃይሎች ጥቃት ሰለባ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ መናገራቸውን መዘግባችን ይታወሳል።
በወረዳዋ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ስራቸው ተስተጓጉሎ የሚገኝ ሲሆን ወረዳዋ በወታደራዊ አስተዳደር ውስጥ ትገኛለች በማለት የጸጥታ አስቸጋሪነቱ ተገልጿዋል። በከተማው የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ የንግድ ድርጅቶች፣ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መዘጋታቸውም ታውቋል።