መስከረም ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊ እልቂት እየደረሰ እንደሆነ የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች፣ ከአጋዚ ወታደሮች እና ከፌደራል ፖሊሶች የሚደርስባቸው ጥቃት ለማምለጥ ወደ ተልተሌና አጎራባች ወረዳዎች እየተሰደዱ ነው። በርካታ ታዋቂ ሰዎች ተይዘው አርባምንጭ እስር ቤት መግባታቸውም ታውቋል።
አራስ ሴቶች ሳይቀር በወታደሮች እየተገደሉ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ አሁንም በርካታ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች ወደ አካባቢው በመግባት ላይ ናቸው።
በሌላ ዜና ደግሞ በአርባምንጭ ከተማ የመስቀልን በአል አስታኮ በተዘጋጀው በአል ላይ የሙዚቃ ድግስ ላይ ህዝቡ እንዳይገኝ ጥሪ የሚያቀርብ ወረቀት እየተበተነ ነው። በአማራ፣ ኦሮምያ፣ በኮንሶና ሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች ዜጎች በግፍ እየተገደሉ የሙዚቃ ዝግጅት ማዘጋጀት ህሊና ቢስነት መሆኑን የሚገልጸው ይህ ወረቀት፣ ህዝቡ በሙዚቃ ዝግጅቱና በባዛሩ ላይ ባለመገኘት ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ያለውን ድጋፍ እንዲገልጽ ጥሪ ያቀርባል።