የኮንሶ ህዝብ መሪዎች እየታደኑ ነው

ኅዳር ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የኮንሶ ህዝብ ያቀረበውን ጥያቄ በሃይል ለመጨፍለቅ ተደጋጋሚ የአፈና እርምጃ ሲወስድ የቆየው የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ፣ ተቃውሞውን ያስተባብራሉ ያላቸውን የአካባቢውን የአገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶች ለመያዝ እንቅስቃሴ በመጀመሩ ብዙዎች ራሳቸውን ለመደበቅ ተገደዋል።

አገዛዙ፣ መሪዎቹን በአሸባሪነት የፈረጃቸው ሲሆን፣ በተገኙበት እንዲያዙ አልያም እንዲገደሉ ትእዛዝ መስጠቱን መንጮች ገልጸዋል። ህጻናት፣ ሴቶችና አዛውንቶች ሳይቀሩ ተፈላጊ ሰዎችን ጠቁሙ እየተባሉ ስቃይ እየደረሰባቸው ነው። በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አሁንም ተፈናቅለው የሚገኙ ሲሆን፣ በርካታ ዜጎችም በእስር ቤት እየተሰቃዩ ነው። እስር ቤቶች በእሰረኞች በመሞላላታቸው እስረኞች መኝታ ቦታ ማጣታቸውን፣ በረሃብ ፣ በህክምና እጦትና በንጽህና ጉድለት እየተሰቃዩ ነው።

የአካባቢው ባለስልጣናት ህዝቡ እርስ በርስ እንዲጣላ የመከፋፈል ስራ እየሰሩ ሲሆን፣ የአለማቀፉ ማህበረሰብ ወይም የሚመለከታቸው አካሎች ቶሎ ጣልቃ ገብተው ካላስተካከሉት ከፍተኛ እልቂት ሊፈጠር ይችላል ሲሉ የአካባቢው ምንጮች አስጠንቅቀዋል።