የኮሎኔል መሀመድ ጋዳፊ ልጅ ሰይፍ አሊ ኢስላም ተፈታ።

ፍራንስ 24 የተሰኘው ሚዲያ እንደዘገበው  በሊቢያ ሳይፍ አሊ ኢስላምን ያሰሩት ኃይሎች እንደለቀቁት ጠበቃው ለዓለም አቀፉ ይወንጀለኞች ፍርድ ቤት በምህጻረ ቃሉ አይ ሲሲ አሳውቋል።

ሳይፍ አሊ ኢስላም አባቱን ጋዳፊን ባስወገደው አብዮት ወቅት ፈጽሞታል በተባለው ወንጀል የሞት እስራት ተፈርዶበት እንደነበር ይታወሳል።

የጋዳፊ ሁለተኛ ልጅ የሆነው ሳይፍ አሊ ኢስላም  ነጻነቱን ያገኘው ባለፈው ሚያዚያ ወር እንደኾነ ጠበቃው ካሪም ካን ትናንት ተናግረዋል።

ሳይፍ  የተፈታውም በዓለማቀፍ ደረጃ እውቅና ባገኘውና በሊቢያ  በፋየል አልፋራጅ የሚመራው የአንድነት መንግስት ከመመስረቱ በፊት የሀገሪቱን የተወሰነ ክፍል ያስተዳድር በነበረው በቶብሩክ ፓርላማ የይቅርታ ህግ መሰረት ምህረት አግኝቶ እንደኾነ  ጠበቃው አብራርተዋል።

ስለነበረው ሁኔታ ከደንበኛቸው ጋር ተነጋግረው እንደነበር የተጠየቁት የሳይፍ ጠበቃ  ሳይፍ ሊቢያ ውስጥ በጥሩና በአስተማምኝ ሁኔታ እንደሚኖር ከመግለጽ ውጭ ዝርዝር ጉዳዮችን ከመናገር ተቆጥበዋል።

 

አባቱን ጋዳፊን ይተካል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው ሳይፍ አሊ ኢስላም  እንደ አውርፓውያኑ አቆጣጠር  በ2011 በአማጽያኑ ሚሊሻዎች  ዚንታን ተብላ በምትጠራው  በተራራማዋ የምዕራብ ሊቢያ ክፍል መያዙ ይታወቃል።

ይሁንና ሳይፍን የያዙት ሚሊሻዎች  በሊቢያ አብዮት ወቅት  ተቃዋሚውችን በመግደል  ወንጀል በሌለበት  የሞት ፍርድ ወደበየነበት  ወደ ትሪፖሊ ፍርድ ቤት እንዲያስተላልፉት የቀረበላቸውን ጥያቄ ውድቅ አድርገውታል።

ከዚህም ባሻገር የትሪፖሊው ፍርድ ቤት ያሳለፈው የሞት ፍርድ ሂዩማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ በዓለማቀፍ የሰብ ዓዊ መብት ተሟጋቾች ተቃውሞ ማስነሳቱ አይዘነጋም።