ኢሳት ((ሃምሌ 12 ፥ 2008)
በአዲስ አበባ ከተማ ለስድስት ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው የኮሌራ ወረርሽኝ በሽታ ስርጭቱ በተለያዩ የመዲናይቱ አካባቢዎች በመዛመት ላይ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማክሰኞ አስታወቀ።
የበሽታው ስርጭት መባባስን ተከትሎ በየክፍለ ከተማው ተቋቁመው የነበሩ ጊዜያዊ የህክምና መስጫ ተቋማት በእጥፍ እንዲያድጉ ተደርጎ 26 መድረሳቸው ታውቋል።
በመጣል ላይ ያለው ዝናብ እስከ ነሃሴ ወር ድረስ ቀጣይ በመሆኑ የበሽታው ስርጭት እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የበሽታውን ስርጭት አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት አስፍሯል።
መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ አለም አቀፍ የግብረሰናይ ድርጅቶችና የተባበሩት መንግስታት ተወካይ ተቋማት የበሽታውን ስርጭት ተጨማሪ ጉዳትን እንዳያደርስ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ መሆናቸው ለመረዳት ተችሏል።
የአጣዳፊ ተቅማትና ትውከት (ኮሌራ) በሽታው በከተማይቱ እያደረሰ ያለውን አጠቃላይ ጉዳት ይፋ ከማድረግ ተቆጥቦ የሚገኘው የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ በበኩሉ መረጃውን ይፋ ማድረጉ በህብረትሰቡ ዘንድ ድንጋጤን ሊፈጥር ስለሚችል የደረሰው ጉዳት ለህዝብ ይፋ እንዳይደረግ አቋም መውሰዱን ገልጿል።
ከአንድ ወር በፊት በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች በመዛመት ላይ ባለው በዚሁ የበሽታ ስርጭት እስከ አሁን ድረስ በትንሹ ስድስት ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ ወደ 2ሺ አካባቢ ነዋሪዎችም ዳግም በበሽታው ተይዘው እንደሚገኙ ታውቋል።
የኮሌራ በሽታ ስርጭት እየተባባሰ ይሄዳል የሚል ስጋት መኖሩን ተከትሎ ተጨማሪ የአስቸኳይ ጊዜ የመጠለያና የዕርዳታ መስጫ ማዕከላት ተቋቁመው እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
የጤና ባለሙያዎች በበኩላቸው በከተማዋ ያለው የንጹህ ውሃ አቅርቦት ችግር ለበሽታው መዛመት ምክንያት መሆኑን በመግለጽ ላይ ሲሆኑ ነዋሪዎች በፈረቃ መድረስ ያልቻለው የውሃ እጥረት በእለት ከእለት የኑሮ እንቅስቃሴያቸው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።
የአዲስ አባባ ከተማ ጤና ቢሮ በኮሌራ በሽታ የተያዙ ሰዎች በጊዜያዊነት ወደተቋቋሙ ማዕከላት ብቻ እንዲሄዱ ቢያሳስብም በርካታ ታማሚዎች የበሽታውን ስርጭት በመፍራት ወደ ግል የህክምና መስጫ ተቋማት በመሄድ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
በዚህም የተነሳ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥርንና እያደረስ ያለውን ጉዳት በአግባቡ ማወቅ እንዳስቻለ የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።