ሐምሌ ፳፮ ( ሀያ ስድስት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስ አበባ በስፋት ሲታይ የነበረው የኮሌራ በሽታ በኦሮምያ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ከተሰራጨ በሁዋላ፣ ከሃምሌ 13 /2008 ዓም. ጀምሮ ደግሞ በሰሜን ሸዋ መከሰቱን ከክልሉ ጤና ቢሮ የወጣው መረጃ አመላክቷል፡፡
ወደ ሰሜን ሸዋ የገባው በሽታ በመንዝ ላሉ፣መንዝ ቀያ፣መንዝ ማማ፣አሳግርት፣በረኸት፣ምንጃር ሸንኮራና ሞጃ ወረዳዎች በስፋት ተሰራጭቷል።
የክልሉ መንግስት መረጃውን ይፋ ባያደርገውም በመንዝ ቀያ ወረዳ አምስት ሰዎች እንዲሁም በአሳግርት ወረዳ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን ከዞኑ የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የቅድመ ጥንቃቄው ደካማ መሆን ችግሩ በቀላሉ እንዲስፋፋ አድርጎታል የሚሉት ባለሙያዎች ፤ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ካላደረገ የመዛመት ፍጥነቱ እንደሚቀጥል ያላቸውን ስጋት ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ደረጃ ሊጠቁ ይችላሉ ተብለው በባለሙያዎች የተጠኑ ሃያ ወረዳዎች ሲሆኑ፤በሰሜን ሸዋ ቀሪ አስር ወረዳዎች ፣በሰሜን ወሎ ሁለት፣ደቡብ ወሎ አራት ወረዳዎች ከፍተኛ ስጋት ላይ መሆናቸውን ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡
በሽታው በተከሰተባቸው ወረዳዎች የሚገኙ ታማሚዎች ከሚጠበቀው በላይ የተጎዱ መሆናቸውን ባለሙያዎች ገልጸዋል።
በክልሉ ያለው የንጹህ መጠጥ ወኃ ሽፋን ዝቅተኛ ከመሆን ጋር ተያይዞ በሽታው በዋናነት ንጹህ ባልሆነ ውኃ መተላለፉም ሌላ ችግር እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በአዲስ አበባ እና በኦሮምያ ያጋጠመው የንጹህ ውሃ እጦት ለበሽታው መነሳትና መስፋፋት አስተዋጽኦ አድርጓል። ገዢው ፓርቲ ኮሌራ በሽታ በይፋ መግባቱን ለመግልጽ ባለመፈለጉ ሌላ ስያሜ ተሰጥቶት እንዲመዘገብና ሪፖርት እንዲደረግ እያደረገ ነው።