(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 17/2011)በደቡብ ኢትዮጵያ ተጨማሪ የክልል ጥያቄዎች በመቅረብ ላይ መሆናቸው ተገለጸ።
ጥያቄዎቹ እየቀረቡ ያሉት የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ወደ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያመራ የክልሉ ምክር ቤት ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ነው ተብሏል።
56 ብሔረሰቦች የሚገኙበትና በ9 ዞኖች በተዋቀረው የደቡብ ክልል ከሲዳማ ዞኖች በተዋቀረው የደቡብ ክልል ከሲዳማ ዞን በተጨማሪ ከወላይታ፣ከከፋ፣ከከምባታ እንዲሁም ከጉራጌ የክልል ጥያቄ እንደቀረበለት ታውቋል።
በደቡብ ክልል ምክርቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ሔለን ደበበ ባለፈው ረቡዕ ህዳር 12/2011 ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጻፉት ደብዳቤ የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድበት ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በህገመንግስቱ አንቀጽ 47 ንኡስ አንቀጽ 3 መሰረት ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድም ሕግ ጠቅሰው ጥያቄውን አቅርበዋል።
በሕገ መንግስቱ መሰረት የክልል ጥያቄውን ተግባራዊ ለማድረግ የሲዳማ ዞን የቀረው ሕዝበ ውሳኔ ማድረግ ብቻ ሲሆን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔውን ማደራጀቱን ተከትሎ የክልል ጥያቄው ምላሽ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
የወላይታ፣የከፋ፣የከምባታና የጉራጌ የክልል ጥያቄዎች ላይ የክልሉ ምክር ቤት ያልተነጋገረበት በመሆኑ ወደ ምርጫ ቦርድ አልተመራም።
በደቡብ ክልል ተጨማሪ የክልል ጥያቄዎች እንደሚኖሩም እየተገለጸ ይገኛል።
በሃገሪቱ ከወሰን ጋር ተያይዞ የሚነሱ ግጭቶችን እንዲሁም የማንነት ጥያቄዎችን ጭመሮ የሃገሪቱ የፌደራል አወቃቀር እንደገና እንዲታይ ግፊቶች በመደረግ ላይ ናቸው።